Logo
News Photo

የባቡር ኢንዱስትሪውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር አ/ማ ፣ የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ እና የድሬደዋ ፖሊ-ቴክኒክ ኮሌጅ የሦስትዮሽ የጋራ የስምምነት ሰነድ ተፈራረሙ፡፡

የጋራ  የስምምነት ሰነድ የፊርማ ስነ-ስርዓት ላይ የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ሼር ካንፓኒ ዋና ስራ አስፋፃሚ ዶ/ር አብዲ ዘነበ እንዳሉት ሶስቱ ተቋማት በጋራ መሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት መፈራረማቸው የባቡር ኢንደስትሪውን ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሳድገው ገልጸዋል፡፡  በተለይም በባቡር ኢንዱስትሪው የሚፈለገውን የሰው ኃይል ከማፍራት አንፃርና  አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማስፋት ረገድ ሦስቱ ተቋማት በቅንጅት ለመሥራት መስማማታቸው ከሀገራችን አልፎ ጎረቤት ሀገራትን ተጠቃሚና በማድረግ እርስ በእርስ የሚያስተሳስር ነው ብለዋል፡፡

የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዮት ሳይንትፊክ ዳይሬክተር የሆኑት ኢንጂነር ቴዎድሮስ ገደፋየ በበኩላቸው በሀገራችን የባቡር ትራንስፖርት ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ እድሜ ያለው ቢሆንም ዘርፉን ሳናዘምነውና ሳናሳድገው በመቅረታችን ዘርፉን ለማስፋፋት አሁንም ድረስ በውጪ ባለሙያዎችና ኩባንያዎች ላይ ጥገኛ እንድንሆን አድረጎናል፡፡

የዛሬው ስምምነት ግን ዘርፉን አንድ እርምጃ ወደፊት የሚያራምድ ነው ያሉት ኢንጂነር ቴዎድሮስ ዩኒቨርሲቲው በተለይም የአፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ ሆኖ መመደቡ በሰው ኃይል ልማትና በጥናትና ምርምር ዘርፉን ለማሳደግ እንድንሰራ መንገድ ይከፍታል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም በስምምነቱ መሰረት ስራዎችን የሚያከናውን የጋራ የቴክኒክ ቡድን ተዋቅሮ በአጭር ጊዜ ወደ ስራ እንደሚገባ አሳውቀዋል።

የድሬደዋ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ ሳሊም ኡስማን በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ኮሌጃቸው ገበያው የሚፈልገውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ከማፍራት አንፃር የተጣለበትን ሀገራዊና ቀጠናዊ ኃላፊነት ለመወጣት East African Skills for Transformation and Regional Integration Project (EASTRIP) ተግባራዊ ለማድረግ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው ከተቋማቱ ጋር ተቀራርበው መስራታቸው በብዙ መልኩ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቻ ገልፀዋል፡፡

በፕሮግራሙ ማጠቃለያ ላይም የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር ድሬዳዋ ቅርንጫፍን አጠቃላይ የስራ እንቅስቃሴ በጋራ ጎብኝተዋል።


Share This News

Comment