የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ አነስተኛ ገቢ ላላቸው ቤተሰብ ልጆች የሚውል የተለያዩ የትምህርት ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገ፡፡
የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግልት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሰለሞን ዘሪሁን የትምህርት ቁሳቁሶቹን ለድሬደዋ ትምህርት ቢሮ ተወካይ ባስረከቡበት ወቅት እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው በማኅበረሰብ አገልግልቱ በርካቶችን ተጠቃሚ ሚያደርጉ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን ገልፀው በተያዘው አዲሱ በጀት ዓመትም የሚሠጣቸውን የማኅበራዊ አገልግልቶች በስፋትም በጥራትም በማሳደግ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ መቀጠሉን አብራርተዋል፡፡
የአሁኑ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍም ዩኒቨርሲቲው ከሚሰጣቸው የማኅበራዊ አገልግሎቶች መካከል አንዱ መሆኑን ጠቅሰው በተደረገው ድጋፍም የኑሮ አቅማቸው እጅግ ዝቅተኛ የሆኑና በተለያዩ ችግሮች ሳቢያ የትምህርት ቁሳቁስ ማሟላት ለማይችሉ ችግረኛ ህፃናት የሚውል መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ወንዲፍራው ደጀኔ በበኩላቸው ለተማሪዎቹ የተደረገው የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ 100 (አንድ መቶ) ደርዘን ደብተር እና 2000 (ሁለት ሺህ) ስክሪፕቶ መሆኑን በዚሁ ወቅት ተናግረዋል፡፡
የድሬደዋ ትምህርት ቢሮን በመወከል የትምህርት ቁሳቁሶቹን የተረከቡት የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አቡበከር አብዶሽ ዩኒቨርሲቲው ላደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን ገልፀው የአሁኑ ድጋፍ እንደ ሀገርና እንደ ድሬደዋ አስተዳዳር አንድም ህፃን ከትምህርት ቤት እንዳይቀር በሚል የተጀመረውን ዘመቻ እንዲሳካ ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
Share This News