Logo
News Photo

ድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ የተለያዩ ርዕሶች ላይ ያተኮረውን የ2015 ዓመት የመጀመሪያው ዙር ሴሚናርን ዛሬ አካሄደ፡፡

ዛሬ ህዳር 10/2015 ዓ.ም. ያልተፈለገ እርግዝናና ተዛማጅ ችግሮቹ፣የናኖ ቴክኖሎጂ ምንነት፣ ጠቀሜታ እና አተገባበር እንዲሁም ብሔራዊ መግባባት እንደ ግጭት አፈታት መሳሪያ በሚሉት ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ ፅሁፎች በመምህራን ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ 

በዚህ ሴሚናር ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳን ዶ/ር ሰለሞን ዘርሁን እንደዚህ ዓይነት መድረኮች የመምህራንን እውቀትና ክህሎት የሚያሳድጉ በመሆናቸው ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስገንዝበዋል፡፡ ዶ/ር ሰለሞን አክለውም ሴሚናሮች በዩንቨርሲቲ ደረጃ በዓመት አራት ጊዜ ማዘጋጀቱ ብቻ በቂ እንደማይሆን ገልጸው በያዝነው ዓመት የሴሚናር መድረኮቹ በትምህርት ክፍሎች ደረጃ ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውና አስፈላጊውን ድጋፍ የሚደረግላቸው መሆኑ አረጋግጠዋል፡፡

ይህን ታሳቢ በማድረግም በዩኒቨርሲቲው በቀጣይ ሴሚናሮችን መዘጋጀት እንዳለባቸው የገለጹት ዶ/ር ሰለሞን የዩኒቨርሲቲው የትምህርት ክፍል ኃላፊዎች ሆኑ መምህራን በመድረኮቹ ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የሚጠበቅባቸውን ይወጡ ዘንድ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የልማትና ብዝነስ ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ተማም አወል የሴሚናር መድረኮች በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ አዳዲስ ርዕሰ-ጉዳዮች  ከመሸራሸራቸው ባሻገር የማህበረሰብን ችግር ሊፈቱ የሚችሉ አቅም ያላቸው የምርምር ስራዎች እንዲበራከቱ መንገድ የሚከፍቱ መድረኮች እንደሆኑ አንሰተዋል፡፡ በመቀጠልም እንደዚህ ዓይነቱ መድረኮች በጣም አስፈላጊና ጠቃሚ ስለሆኑ የበጀት እጥረት ቢኖርብንም ውጪን በቆጠበ መልኩ እናዘጋጃለን ብለዋል፡፡

በመጨራሻም መድረኩን ሲመሩ የነበሩት የማህበረስብ እና ስነ-ሰብ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን የሆኑት ዶ/ር አለማየሁ ዘውዴ መድረኩ ብዙ ግንዛቤ የተገኘበት መሆኑን ገልጸው መምህራን ሴሚናሮችን በማቅረብም በመሳተፍም የመማማሪያ መድረኮቹን የበለጠ ማጠናከር እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡ 

ለአንድ ቀን በቆየው ሴሚናር ላይ በድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ደረጃዎች ላይ የሚገኙ አመራሮች፤ ተመራማሪዎች እና መምህራን ተሳታፊ ሆነውበታል፡፡

Share This News

Comment