Logo
News Photo

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ሰራተኞች የእግር ኳስ ጤና ቡድን ከወራቤ ዩኒቨርሲቲ ሰራተኞች እግር ኳስ ጤና ቡድን ጋር የወዳጅነት ግጥሚያ አደረገ፡፡

የወራቤ ዩኒቨርሲቲ የጤና ቡድን ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ጤና ቡድን በቀረበለት ጥሪ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በመገኘት ባደረገው ጨዋታ 1 ለ 0 በሆነ ውጤት በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ አሸናፊነት ጨዋታው ተጠናቋል፡፡ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የሰራተኞች የእግር ኳስ ጤና ቡድን ዩኒቨርሲቲው ከተቋቋመ ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ ተቋሙን በመወከል ከተለያዩ ተቋማት ጤና ቡድን ጋር ጨዋታዎችን እያከናወነ ያለ ሲሆን በዛሬው ዕለትም ከአቻው ከወራቤ ዩኒቨርሲቲ የሰራተኞች እግር ኳስ ጤና ቡድን ጋር ጨዋታውን አድርጓል፡፡ ጨዋታውን ያስጀመሩት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት እና የወራቤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት በሜዳ ተገኝተው ጨዋታውን አስጀምረዋል፡፡  የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶ/ር ኡባህ አደም ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ወደ በረሃዋ ንግስትና የኢንዱስትሪ ኮሪደር ወደሆነችው ድሬዳዋ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ዶ/ር ኡባህ አያይዘው ዩኒቨርሲቲያችን ከዚህ ቀደም በተለያዩ ተቋማት በመገኘት የጤና ቡድኑ የተለያዩ ጨዋታዎችን ሲያደርግ እንደቆየና በዛሬው ዕለትም ከአቻው ከወራቤ ዩኒቨርሲቲ የወዳጅነት ጨዋታውን ሲያደርግ የክቡር ዶ/ር አርቲስት አሊ ብራን መታሰቢያ ምክንያት በማድረግ እንደሆነ አንስተው በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው ለዶ/ር አርቲስት አሊ ብራን ስራዎች ለመዘከር እና በእሳቸው ስም የተለያዩ ስራዎች እንደሚደረጉም ጠቁመዋል፡፡ 

የወራቤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር እንጂነር ቶፊቅ ጀማል የወራቤ ዩኒቨርሲቲ የሰራተኞች እግር ኳስ ጤና ቡድን ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የሰራተኞች እግር ኳስ ጤና ቡድን ጋር የወዳጅነት ጨዋታቸውን ለማድረግ የፍቅር ከተማ ወደ ሆነችው ድሬዳዋ መገኘታቸው እጅግ እንዳስደሰታቸው ገልጸው የጨዋታው አላማ የክቡር ዶ/ር አሊ ቢራ መታሰቢያ መሆኑ ደግሞ እጅግ ደስታ እንደፈጠረላቸው ባደረጉት የጨዋታው መክፈቻ ላይ ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር እንጂነር ቶፊቅ አያይዘው ዶ/ር አሊ ብራ በኢትዮጵያኖች ዘንድ እጅግ ተወዳጅ የጥበብ ሰውን በዚህ መዘከራችን ኩራት እንደሚሰማቸው ገልጸው በቀጣይም ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ጋር ተባብረው ለመስራት ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸው፤ ጨዋታውን ከወራቤ ዩኒቨርሲቲ ከመጡ ም/ፕሬዝዳንቶችና አመራሮች ጋር በድሬዳዋ ተገኝተው ጨዋታውን መከታተላቸው ደስታ እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል፡፡ 

ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በድሬዳዋ ከተማ በየዓመቱ በድሬዳዋ አስተዳደር ስፖርት ኮሚሽን አዘጋጅነት በተቋማት መካከል በሚደረገው ውድድር ላይ ዩኒቨርሲቲው በቋሚነት ሲሳተፍ መቆየቱ ይታወቃል። 


Share This News

Comment