Logo
News Photo

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ አፍ-ሱማሌ ቋንቋ ትምህርት ክፍል የኪነጥበብ እና የስነ-ጽሁፍ ፕሮግራም አዘጋጀ።

ፕሮግራሙ ለይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም እንደገለፁት አፍ-ሱማሌ ቋንቋና ባህል እንዲያድግ እንደዚህ ያሉ ፕሮግራሞች መዘጋጀታቸው የሚበረታታ እንደሆነ ገልፀው ቋንቋውን ለማሳደግ ዩኒቨርሲቲው ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ አንደሆ ገልጸዋል፡፡
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ አፍ-ሱማሌ ቋንቋ ትምህርት ክፍል ባዘጋጀው የስነ-ጽሁፍ ፕሮግራም ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር መገርሳ ቃሲም እንደገለፁት ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር የጀመረው ትምህርት ክፍሉ ለሶማሊኛ ቋንቋ ማደግ እያበረከተ ያለው አስተዋፅኦ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ነው ብለዋል፡፡
ይህንኑ ታሳቢ በማድረግም በአዲሱ የ2014 ዓ.ም ከዚህ ቀደም ሲሰጥ ከነበሩት የመደበኛና የክረምት የትምህርት ክፍለ ጊዜዎች በተጨማሪ በእረፍት ቀናትም ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን አስረድተዋል፡፡
የአፍ-ሱማሌ ቋንቋ የትምህርት ክፍል ኃላፊ የሆነቱ አቶ ጉሌድ ከድር በበኩላቸው ትምህርት ክፍሉ እስካሁን ስልሳ ሰባት (67) ተማሪዎችን በመደበኛ እና ስልሳ አራት (64) ተማሪዎችን ደግሞ በክረምት መርሐግብር ማስመረቁን ጠቅሰው በ2014 ዓ.ም በስራቸው ባህሪ ሳቢያ የትምህርት አድል ለማግኘት ለተቸገሩ የድሬዳዋና አካባቢዋ ነዋሪዎች የእረፍት ቀን ክፍለ ጊዜ መመቻቸቱን ተናግረዋል፡፡
አቶ ጉሌድ አክለውም ትምህርት ክፍሉ በማኅበራዊ አገልግሎት በአፍ-ሱማሌ ቋንቋ የአሽከርካሪነት የጽሁፍ ፈተና እንዲዘጋጅ ማድረጉን እንዲሁም የኢሳ ማህበረሰብ የአስተዳደር ስረዕት( ሄር) ላይ በጥናት የተደገፈ ምርምር በማድረግ ይህን ባህላዊ ቱፊት ለማሳደግና ለማስተዋወቅ በእንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝም አብራርተዋል፡፡
ፕሮግራሙ ላይ ተገኝተው መልዕክታቸውን ያስተላለፉት የድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሃለኔ ሃሰን ዩኒቨርሲተው የአፍ-ሱማሌ ቋንቋና ባህል ለማሳደግ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ አድንቀው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልፀው ቢሯቸውም ከትምህርት ክፍሉ ጋር ተቀራርቦ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡
በመጨረሻም በዝግጅቱ ላይ የተገኙት የሶማልኛ ቋንቋ የክረምት ክፍለ ጊዜ ተመራቂ ተማሪዎች ከኪሳቸው ባዋጡት 4 ሺህ ብር የገቢ አቅማቸው ዝቅተኛ ለሆኑ ህፃናት ተማሪዎች የንጽህና መጠበቂያ ድጋፍ አድርገዋል፡፡

Share This News

Comment