Logo
News Photo

"ሀገር በቀል እውቀቶች ላይ መሠረት ያደረጉ የምርምር ስራዎች ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ" በሚል ርዕስ 8ኛው ዙር ሀገር አቀፍ ኮንፈረንስ በማህበራዊ ሳይንስና ስነሰብ ኮሌጅ አዘጋጅነት ተካሄደ፡፡

በኮንፈረንሱ ላይ በመገኘት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በዩኒቨርሲቲው የቢዝነስና ልማት ም/ፕሬዝዳንትና የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ተወካይ ዶ/ር ተማም አወል የጀመርነው ፈጣን ልማትና እድገትን የሚፈለገው ግብ ላይ አድርሰን ህዳሴያችን ህውን ማድረግ የምንችለው ከሁሉም በፊት የአገራችን ሰላም በዘላቂነት መረጋገጥ ስንችል  ነው፡፡

"ለዚህ ደግሞ እያንዳንዳችን ከሰፊው ተልዕኮ የድርሻችንን ቆርሰን በመውሰድ ግዴታችንን መወጣት ስንችል  ያለምነውን ዘላቂነት ያለው  አስተማማኝ  ሰላምና እድገትን ማሳካት የምንችለው " ያሉት ዶ/ር ተማም ሁላችንም የተጣለብንን ግዴታ መወጣት ይገባናል ብለዋል ፡፡

በተለይ ደግሞ  ምሁራን ለአገራችን ሰላም በዘላቂነት መረጋገጥ ከፍተኛ እገዛ የሚኖራቸውን የሀገር በቀል እውቀቶቻችንን መሠረት ያደረጉ የጥናትና የምርምር ስራዎችን በማበርከት የበኩላቸውን ይወጡ ዘንድ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

በኮንፈረንሱ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት በዩኒቨርሲቲው የምርምርና የማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሰለሞን ዘሪሁን በዩኒቨርሲቲው ካለፋት ተከታታይ ሁለት ዓመት ወዲህ የመምህራን በምርምር ሥራዎች ላይ ያላቸው ተሳትፎ እያደገ  መጥቷል፡፡ 

ለዚህ ውጤት መገኘት ደግሞ ከባለፈው ሁለት ዓመት ወዲህ በቢሯቸው በኩል   የተፈጠሩ ምቹ ሁኔታዎች የራሳቸው የሆነ አወንታዊ ድርሻ የነበራቸው መሆኑን የገለፁት ዶ/ር ሰለሞን በቀጣይም የመምህራኑን በምርምር ሥራዎች ላይ የመሳተፍ ድርሻ አሁን ካለበት ደረጃም ከፍ ለማድረግ ከቀድሞ በበለጠ ትኩራት ተሰጥቶበት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡

ኮንፈረንሱ አስመልክተው ገለፃ ያደረጉት በዩኒቨርሲቲው የማኅበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር አለማየሁ ዘውዴ በበኩላቸው ኮንፈረንሱ "ሀገር በቀል የምርምር ስራ  ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ" በሚል ርዕስ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ለ8ኛ ጊዜ በኮሌጅ ደረጃ ደግሞ ለ3ኛ ጊዜ ተዘጋጀ መሆኑን ጠቅሰው ሀገር አቀፍ ኮንፈረንሱ በተለይ ወጣት የዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎች ልምድ የሚቀስሙበትና የሚማማሩበት ይሆናል ፡፡

ዶ/ር አለማየሁ አክለውም እስከዛሬ በኮሌጃችን 19 የተጠናቀቁ  የምርምር ስራዎችን ማቅረብ ከመቻላችን ባሻገር ካለፈው ሁለት ዓመት ወዲህ መምህራኖቻችን በድሬደዋ አስተዳደር በተዘጋጁ  ትልልቅ  አገራዊ መድረኮች ላይ ለውይይት መነሻ የሚሆኑ ጥናታዊ ጽሁፎችን በማቅረብ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም በማስፈን ሂደት ውስጥ የበኩላቸውን አሰተዋፅኦ ሲያበረክቱ መቆየታቸውን እና ይሄም እንቅስቃሴ ተጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል፡፡

ለአንድ ቀን በቆየው ኮንፈረንስ ላይ በሀገር በቀል እውቀቶች ላይ በርካታ ጥናትና ምርምር ያደረጉት ታወቂው ምሁር አቶ አብዱልፈታ አብደላ ሀገርበቀል እውቀቶች ለዘላቂ ሰላምን መስፈን ያላቸውን ፋይዳ አስመልክተው ቁልፍ መልዕክታቸውን ለኮንፈረንሱ ታዳሚዎች አስተላልፈዋል፡፡ በኮንፈረንሱ ላይ 7 ሀገርበቀል እውቀቶች ለሰላም የሚኖራቸውን ፋዳ አስመልክቶ በድሬደዋ ዩኒቨርሲቲና ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች በመጡ ምሁራን ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት የዩኒቨርሲቲያችን ትክክለኛ የማህበራዊ ትስስር ገፆች Like እና Subscribe በማድረግ ይከታተላሉ፡-

Share This News

Comment