Logo
News Photo

በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የስራ ዕድል ፈጠራ ክህሎት ላይ ያተኮረ ስልጠና ለተማሪዎች መስጠት ጀመረ፡፡

የካቲት 27/2015 ዓ.ም ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ከትምህርት ሚ/ር፣ ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚ/ር እና ከተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ድርጅት UNDP ጋር በመተባበር ከ2ኛ  እስከ 4ኛ አመት ላሉ ወደ ቢዝነስ እና ኢንኩቤሽን ማዕከል ለሚገቡ ተማሪዎች በስራ ዕድል ፈጠራ ላይ ያተኮረ ስልጠና መስጠት መጀመሩን ገለጸ፡፡ በስልጠናው መክፈቻ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ዶ/ር መገርሳ ቃሲም የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝዳንት እና የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ተወካይ ከሚኒስቴር መ/ቤቶች እና ከተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ተወካዮች፣ ለአሰልጣኞችና ለሰልጣኝ ተማሪዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር አድርገዋል፡፡ ዶ/ር መገርሳ ቃሲም እንደገለፁት መንግስት በአገር አቀፍ ደረጃ በስራ ዕድል ፈጠራ የጀመረውን ንቅናቄ እውን ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎችን በመደጋገፍ እና በትብብር ላይ የተመሰረተ ስራ መሰራት እንዳለበት ገልጸው ለዚህ ስልጠና የተመረጡ ተማሪዎችም ይህን ዕድል እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅመው የሚሰጣችሁን ስልጠና በጥብቅ ዲሲፕሊን እንዲከታተሉ እንዲሁም የፈጠራ ስራዎቻቸው የማህበረሰባችን ችግር ሊፈቱ የሚችሉ መሆን እንዳለባቸውና በቀጣይ ለሚጠብቃቸው እድሎች ሙሉ ዕውቀትና ዝግጅት ይዘው እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትብብር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር እሸቱ መኮንን ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በሃገሪቱ ካሉት ዩኒቨርሲቲዎች መካከል ከሶስቱ አንዱ ሆኖ እድሉን ማግኘቱን አመስግነው፣ ይህ የስልጠና እድል መገኘቱ ምቹ የስራና የንግድ ቀጠና ለሆነችው ድሬዳዋ ትልቅ ግብዓት እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡  ዶ/ር እሸቱ መኮንን አያይዘው ተማሪዎቹ የተመረጡበት ሂደት ስያስረዱ 250 ተማሪዎች በማስታወቂያ ጥሪ ተደርጎላቸው እንደተመዘገቡና ከእነዚህ ውስጥ 50 የሚሆኑት ኢንኩቤሽን ማእከሉን መስፈርት አማልተው ለዚህ ስልጠና እንደበቁ ተናግረዋል፡፡ ስልጠናውም ቀጣይነት እንዳለው አስረድተው ተማሪዎቻችን ባገኙት ዕድል ተጠቅመው የፈጠራ ሀሳባቸውን ከስልጠናው በሚያገኙት ክህሎት አዳብረው ለተሻለ ነገ እንዲዘጋጁ መክረዋል፡፡

ወ/ሪት ፍሩት ኃይሉ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚ/ር እና የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ድርጅት ተወካይ በስልጠናው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር የዚህ ስልጠና አገራዊ ዓላማው ስያብራሩ መንግስት ያስቀመጠው የልማት ፕሮግራም እውን ለማድረግ ሰዎች የፈጠራ ሀሳብ ይዘው ወደ ቢዝነስ እንዲገቡ ለማስቻል እና ከውጪ የቴክኖሎጂ ጥገኝነት ተላቀው ሀገራቸውን ባላቸው የፈጠራ ችሎታ ማዳበር እንዲችሉ ለማድረግ እንዲሁም ተማሪዎች ከመንግስት እጅ ከመጠበቅ ይልቅ በራሳቸው አቅም ሀሳባቸውን እውን እንዲያደርጉ በአገር አቀፍ ደረጃ ካሉት ዩኒቨርሲቲዎች ድሬዳዋን ጨምሮ ሶስት ዩኒቨርሲቲዎች እንደተመረጡ፤ተማሪዎች የስልጠና ዕድሉን ተጠቅመው ዕውቀታቸውን እንዲያጎለብቱ ሚኒስቴር መ/ቤቱ እና የልማት ድርጅቱ ድጋፍ እንደማይለያቸው ገልጸዋል፡፡

Share This News

Comment