በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የስራ ዕድል ፈጠራ ክህሎት ላይ ትኩረት ያደረገ ላለፋት 7 ተከታታይ ቀናት ለተማሪዎች ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ተጠናቀቀ፡፡
ከየካቲት 27 እስከ መጋቢት 03 ቀን 2015 ዓ.ም የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የትምህርት ሚኒስቴር፣ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና ከተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ድርጅት ጋር በመተባበር በድሬዳዋ ፣በባህርዳር እና በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲዎች ወደ ቢዝነስ እና ኢንኩቤሽን ማዕከል ለሚገቡ ተማሪዎች በስራ ዕድል ፈጠራ ላይ ያተኮረ ስልጠና ሲሰጥ ነበር የቆው፡፡
በስልጠናው መዝጊያ ላይ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚንስትር ዶ/ር በለጠ ሞላ በቨርችዋል የቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝንት ባደረጉት ንግግር መንግስት ህዝባችን ካለበት ስር የሰደደ ድህነት ተላቆ ኑሮው እንዲሻሻል የሳይንስና ቴክኖሎጂው ዘርፍ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ገልፀው የአሁኑ ስልጠናም የዚሁ ፕሮግራም አንድ አካል ነው ብለዋል፡፡
ስልጠና እድል ያገኙ የዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚደንቶችም በቨርቹዋል ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲያችን የቢዝነስ እና ቴክኖሎጂ ኢንኩቤሽን ማዕከል በዚህ ዓመት ከፍቶ ስራ የጀመረ ሲሆን ያገኘነው የስልጠና እድል ለማዕከሉ ትልቅ ግብዓት እንደሚሆን ገልጸው ዩኒቨርሲቲውም በከፍተኛ ቁርጠኝነት ማዕከሉን በተገቢው ደረጃ ለማደራጀት ይሰራል ብለዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ መንግስትም በአገር አቀፍ ደረጃ በስራ ዕድል ፈጠራ የጀመራቸው እንቅስቃሴዎች ግባቸውን እንዲመቱ ዩኒቨርሲቲው የበኩሉን ይወጣል ያሉት ዶ/ር ኡባህ የማኅበረሰባችንን ችግር በዘላቂነት መፈታት እንዲችልም ስራ ጠባቂ ብቻ ሳይሆን ስራ ፈጣሪ የሆኑ ብቁ ባለሞያዎችን በማፍራት ረገድ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በስልጠናው ለመሳተፍ ፍላጎት ከነበራቸውና ከተመዘገቡ ከ250 ተማሪዎች መካከል የኢንኩቤሽን ማእከሉን መስፈርት አሟልተው 50 ተማሪዎች ለዚህ ስልጠና እንደበቁ የተገለጸ ሲሆን ከእነርሱን መካከል 29 ወንዶች እና 23 ሴቶች ናቸው ፡፡
በመጨረሻም ስልጠናውን ለተከታተሉ ተማሪዎችም የምስክር ወረቀት ከድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ እጅ ተበርክቶላቸዋል፡፡
Share This News