Logo
News Photo

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ግምቱ ከ1.4 ሚሊየን ብር በላይ የሆነ የምግብ ቁሳቁስ ድጋፍ በኦሮምያ ክልል ቦረና ዞን በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ አደረገ፡፡

በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል በቦረና ዞን በዝናብ እጥረት ሳቢያ በተከሰተው ድርቅ ቁጥሩ 8 መቶ ሺህ የሚጠጋ ህዝብ ለከፋ የምግብ እጥረት መጋለጡ ሲነገር መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡

ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት ለወገን ደራሽ  ወገን ነው በሚል የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል። ድጋፉ ከመምህራን፣ ከአስተዳደር ሰራተኞች እና ከተማሪዎች የተሰበሰበ የገንዘብ ድጋፍ ሲሆን ዩኒቨርሲቲው እንደተቋም የአንድ ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡

በድምሩ 1.4 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ የዳቦ ዱቄት ግዢ በመፈፀም ለዚህ ተግባር የተቋቋመው የኮሚቴ ተወካዮች እና የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር አብርሃም እውነቱ በተገኙበት በነገሌ ቦረና ከተማ የድጋፍ ርክክብ ተፈጽሟል። 

በዚሁ ወቅት የዩኒቨርሲቲው  የአስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር አብርሃም እውነቱ እንደገለጹት መላው የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ከከዚህ ቀደም አገር ለምታቀርበው ጥሪ አፋጣኝ ምላሽ ሲሰጥ መቆየቱን አንስተው በቦረና ዞን በድርቅ ሳቢያ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖችም ጥሪውን በመቀበል የተደረገ ድጋፍ የተደረገ ሲሆን በቀጣይም የሚደርገውን ድጋፍ በቻላው አቅም ሁሉ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

ድጋፉን የተረከቡት የኦሮምያ ብሔራዊ ክልል የቦረና ዞን ከፍተኛ አመራሮችና የክልሉ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮምሽን ቢሮ ኃላፊዎች "በዚህ በአስቸጋሪ ወቅት ህዝባችን የገጠመውን ፈተና መቋቋም እንዲችል ዩኒቨርሲቲው እና መላው የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ከጎናችን በመሆን ላበረከተልን ድጋፍ በቦረና ዞን ህዝብ ስም ምስጋናችንን አናቀርባለን " በማለት ተናግረዋል፡፡

Share This News

Comment