Logo
News Photo

የቴክስታይል፣ አፓረል እና ፋሽን ዲዛይን ት/ቤት ሁለተኛዉን ሃገር አቀፍ ኮንፈረንስ አካሄደ፡፡

በዚሁ ኮንፈረንስ ተገኝተው የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የቴክስታይል፣ አፓረል እና ፋሽን ዲዛይን ት/ቤት ዲን የሆኑት አቶ አማረ ወርቁ  ሲሆኑ በንግግራቸውም ይህ የሃገር አቀፍ አውደ ጥናት   ዋና ዓላማ  ተቋማት ከተቋማት ትስስር ለማጠንከር፣  አብሮ ለመሰራት እና የመተጋገዝ ባህልን ለማሳደግ እንዲሁም በጋራ የሚሰሩ  ምርምሮችም አብሮ ለማስራት መንገድ የሚከፍት  ነው ሲሉ  ገልጸዋል፡፡ 


አቶ አማረ ወርቁ  ለተሳታፊዎች በንቃት እንዲሳተፉ ካሳሰቡ በኋላ የመክፈቻ ንግግር እንዲያደረጉ የኢንስቲትዩቱ ማኔጂንግ ዳይሬክተር የሆኑትን አቶ ጌቱ ግርማን በመጋበዝ ንግግራቸው ዘግተዋል፡፡

አቶ ጌቱ ግርማ በመክፈቻ ንግግራቸው  የቴክስታይል፣ አፓረል እና ፋሽን ዲዛይን ት/ቤት  በኢንስቲትዩቱ ስር ከሚገኙ  ት/ቤቶች አንዱ ሲሆን ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ቴክስታይል ምህንድስና እንዲሁም ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ አፓረል እና ፋሽን ዲዛይን ት/ክፍሎችን በመክፈት በመጀመሪያ ድግሪ በማስተማር ላይ ይገኛል ካሉ በኋላ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖጂ ኢንስቲትዩትም ለዚህ ት/ቤት ልዩ ትኩረት በመስጠት የቤተ-ሙከራ ግብዓቶችን በማሟላት ላይ ይገኛል ሲሉ ገልጻዋል። አቶ ጌቱ ግርማ በተጨማሪ እንደሀገርም ቢሆን መንግስት ቅድሚያ ትኩረት ተሰቷቸው እየተሰሩ ካሉ ኢንዱስትሪዎች መካከል አንዱ የቴክስታይል ዘርፍ በመሆኑ እና ድሬዳዋ የኢንዱስትሪ ከተማ በመሆኗ የቴክስታይ ፣ አፓረል እና ፋሽን ዲዛይን ት/ቤት ከኢንዱስትሪዎች ጋር ትስስር ፈጥሮ ለመስራት ምቹ አጋጣሚ መሆኑን ጠቁመው ት/ቤቱ በምርምር ፤በማህበረሰብ አገልግሎት እና ቴክኖሎጂ ሽግግር  በንቃት እየሰራ በማውሳት ይህን ስራውን በተሻለ ደረጃ ያሳድግለት ዘንድ በዛሬው ዕለት የሚካሄድው የመጀመርያው ዓመታዊ  ሃገር አቀፍ ዓውደ-ጥናት ማካሄዱ  ወሳኝ መሆኑ በመግለጽ ንግግራቸው ቋጭተዋል። 


በኮንፈረንሱ መርሃ ግብር ተገኝተው የመጀመርያው ቁልፍ መልእክት ያስተላለፉት የቀድሞው የEiTEX ሳ/ዳይሬክተር, (ባ/ህ/ዩ)  እና በተለያዩ የስራ ተሳትፎ የሚታወቁትን በአንጋፋነት የሚታወቁትን  ተ/ፕ ዶ/ር አበራ ከጪ ሲሆኑ በንግግራቸው ፕሮግራሙን ለማዘጋጀት ድጋፍ ላደርጉ የዩኒቨርስቲው አመራሮች፣ ለዩንቨርሲቲው ማህበረሰብ እና ኮንፈረንሱን  ላዘጋጀው ት/ቤት   ታላቅ ምስጋና አቅርበዋል። 

ተ/ፕ ዶ/ር አበራ ከጪ በዘርፉ በማምረት አቅም ያሉበት ደረጃ፣ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች እና ለወደፊቱ ዉጤታማ ለማድረግ ምን መሰራት እንዳለበት በቁልፍ መልዕክታቸው ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም ተ/ፕ ዶ/ር አበራ ከጪ በተለያዩ የአለም ሀገራት ያሉ የቴክስታይል ዘርፎችን ዳሰዋል፡፡ የመጀመርያው ዘመናዊ የጨርቃጨርቅ ፋብሪካ በድሬዳዋ እንደተከፈተ በማውሳት የእለቱን ቁልፍ መልእክት “ኢትዮጵያ ታምርት” የሚለውን መሪ ቃል በማንሳት እንዴት ታምርት፣ ለማን ታምርት፣እና የራሳችን ሃብት ተጠቅመን  ከማምረት አንጻር የሚደረገውን ርብርብ ከጨርቃጨርቅ ዘርፉ አኳያ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን በተለይም ፖሊሲንና ኢንዳስትሪዎችን ትኩረት ተሰጥቶባቸው እየተሰሩ እንደሆነ ለኮንፈረንሱ ታዳሚዎች ሰፋ ያለ ማብራርያ  ሰጥተዋል። 


በኮንፈርንሱ አምስት የምርምር ስራዎች ቀርበው ከታዳሚዎች የተለያዩ ጥያቄዎች እና አስታያየት የተነሱ ሲሆን ጥናታዊ ጽሁፍ አቅራቢዎቹም ሰፋ ያለ ምላሽ እና ማብራርያ ሰጥተዋል። ከዚህ በመቀጠል እንደ አጠቃላይ የቴክስታይል ዘርፉን በተመለከተ ዉይይት የተካሄደ ሲሆን የማጠቃለያ ሃሳብ ተሰጥቶበታል። 


በመጨረሻም በአፓረል እና ፋሽን ዲዛይን ት/ክፍል ተመራቂ ተማሪዎች ዲዛይነርነት፣ በዩኒቨርሲቲው በተለያየ ዲፓርትመንት በተዉጣጡ ሞዴሎች፣ እና በት/ክፍሉ መምህራን የፋሽን ሾው ታካሂዷል፡፡ ለፋሽን ሾው ዝግጅትም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እና ንጉስ ከአልኮል ነፃ መጠጥ ስፖንሰር አድርገዋል፡፡


በማጠቃለያ መርሀ ግብሩ የድሬ ዳዋ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ባደረጉት ንግግር አዘጋጆችን እና ተሳታፊዎችን አመስግነው ት/ቤቱ ተስፋ የተጣለበት በመሆኑ የሚያስፈልገውን ግባት ለማሟላት ቁርጥኛ መሆናቸውን እና በዝግጅቱ እጅግ ደስተኛ እንደሆኑ  ገልጸዋል።


የኮንፈረንሱን የመዝጊያ ንግግር  ያደረጉት የቴክስታይል፣ አፓረል እና ፋሽን ዲዛይን ት/ቤት ዲ/ን የሆኑት አቶ አማረ ወርቁ በንግግራቸው ለኮንፈረንሱ የምርመር ስራ አቅራቢዎች፣ተጋባዥ እንግዶች፣ ተሳታፊዎች እንዲሁም ዝግጅቱ ያማረ እና የተሳካ እንዲሆን ብርቱ ጥረት ላደረጉ ሁሉም የኮሚቴ አባላት ከፍ ያለ ምስጋና አቅርበዋል። በመጨረሻም በዝግጅቱ ለተሳተፉ፣ ከተለያዩ ኢንደስትሪ ለተሳተፉ ፣ በት/ቤታቸው ለሚገኙ መምህራን እና ተማሪዎች እነዲሁም ለፋሽን ሾው ዝግጅት ስፖንሰር ላደረጉት በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እና ንጉስ ከአልኮል ነፃ መጠጥ ከፍ ያለ ምስጋና በማቅረብ ኮንፈረንሱን ቋጭተዋል፡፡

Share This News

Comment