Logo
News Photo

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በክቡር ዶ/ር አርቲስት አሊ ቢራ  ስም ግዙፍ ዘመናዊ ቤተ-መጽሐፍት፣ የነፃ የትምህርት ዕድል (Scholarship) እና የኪነ-ጥበብ ትምህርት ክፍል መሰየሙን ዛሬ አርቲስቱን ለመዘከር በተዘጋጀው ስነ-ስርዓት ላይ አስታወቀ፡፡

በዛሬው እለት በድሬዳዋ ከተማ በቢ-ካፒታል ሆቴል ባለፈው መስከረም 28 ቀን 2015 ዓ.ም ባደረበት ህመም ምክንያት ከዚህ ዓለም በሞት የተለየውን ክቡር ዶ/ር አርቲስ አሊ ቢራን ለማሰብ የድሬዳዋ ዩኒቨርሰቲ ባዘጋጀው የዝክር ፕሮግራም ላይ የዩኒቨርሲቲውን ከፍተኛ አመራሮች ጨምሮ ፣ ታወቂ አርቲስቶች ፣ ስመ ጥር የሙዚቃ ሰዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታዳሚ ሆነውበታል፡፡

የፕሮግራሙን ታዳሚዎች እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም ክቡር ዶክተር አርቲስት አሊ ቢራ ለኦሮሞ ባህል፣ ቋንቋ እና ሙዚቃ እድገት ፈርቀዳጅ ድምፃዊ ከመሆኑም በላይ በዘመን ተሸጋሪ ሥራዎቹ ፍቅርን፣ ሰላምን፣ ነፃነትን፣ እኩልነትን እና አንድነትን በህይወት ዘመኑ ሁሉ ሲሰብክ የኖረ ታላቅ አርቲስት ነው ብለዋል፡፡

የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ይህ ታላቅ አርቲስት ለአገር ሁለንተናዊ እድግት የነበረውን አበርክቶ ከግምት ውስጥ በማስገባት በ2011 ዓ.ም የክቡር ዶክትሬት ዲግሪ ያበረከተለት ሲሆን በዛሬው እለትም እሱን ለመዘከር በተዘጋጀው የማስታወሻ ፕሮግራም ላይ በአርቲስቱ ስም በአሁኑ ሰዓት 90 በመቶ ግንባታው የተጠናቀቀውና በአንድ ጊዜ 4 ሺህ ሰዎችን ማስተናግድ የሚችለውን ግዙፍና ዘመናዊ ቤተ- መጽሐፍት፣ በየዓመቱ የሚሰጥ ነፃ የትምህርት እድል (Scholarship) እና የኪነ-ጥበብ የትምህርት ክፍል በስሙ እንዲሰየም የዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት መወሰኑን አስታውቀዋል፡፡

በድሬደዋ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ መዕረግ የመንግስት ተጠሪ የተከበሩ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ  በበኩላቸው የሃቅ ፣የመብት ፣ የሰላም አና የበጎ ስራዎች ታጋይ የሆነው ክቡር ዶክተር አርቲስት አሊ ቢራ ከሙዚቃው በዘለለ በማኅበራዊው ዘረፍ ላይ በመሳተፍ በርካታ በአስተዳደሩ ገጠር ቀበሌዎች የሚገኙ ህፃናት የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ በማድረግ ያበረከተው አስተዋፅኦ ሁሌም የሚወሳለት ነው ብለዋል፡፡

በዚሁ የማስታወሻ ፕሮግራም ላይ የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማኅበር ፕሬዝዳንት ታወቂው የሙዚቃ ሰው  ዳዊት ይፍሩ አሊ ቢራ ካበረከተው ዘመን አይሽሬ ሙዚቃዎቹ ጎን ለጎን የቅጂ መብት እንዲከበር በተለይም በ1997 ዓ.ም በርካታ የአገራችን አርቲስቶች አደባባይ ወጥተው ድምፃቸውን ሲያሰሙ ኢሊ ቢራ የነበረው አስተዋፅኦ ከፍተኛ የነበረ በመሆኑ ማኅበሩ በዚህ አበርክቶው ሁሌም ያስታውሰዋል ብለዋል፡፡

ታዋቂው የሙዚቃ ሰውና የአዲስ አበባ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሰርፀፍሬ ስብሀት በዚሁ ፕሮግራም ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ለሀገር ባለውለታ ለሆነው አርቲስት የሰጠው እውቅና እና ክብር ሊያስመሰግነው እንደሚገባ ገልጸው ሌሎች መሰል የትምህርት ተቋማትም ይህንኑ አርያ ሊከተሉ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ 

በፕሮግራሙ ላይ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የፕሬዝዳንት አማካሪ ክቡር መሐመድ ቆጴ፣ የክቡር ዶክተር አርቲስት አሊ ቢራ ባለቤት ሊሊ ማርቆስ (ኢሊሊ ቢራ)፣ ታወቂዎቹ የኦሮምኛ ሙዚቃ ድምፃዊያኑ ቀመር ዩሱፍ እና ታደለ ገመቹ መልዕክቶቻቸውን አስተላልፈዋል፡፡

Share This News

Comment