Logo
News Photo

የመውጫ ፈተና ተጠናቀቀ።

ካለፈው ሰኔ 30 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ለተመራቂ ተማሪዎች ሲሰጥ የነበረው የመውጫ ፈተና በተያዘው መርሀግብር መሠረት ያለ ምንም ችግር መጠናቀቁን በዩኒቨርሲቲው የቅበላና አካዳሚክ ሪከርድ አልሙኒ ዳይሬክቶሬት አስታውቋል፡፡

የዳይሬክቶሬቱ ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ጅብሪል አብዱልቃድር እንዳስታወቁት ካለፈው ከሰኔ 30 ቀን አስከ ዛሬ አርብ ሐምሌ 07 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ  በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ሲሰጥ የነበረውን 51 የትምህርት አይነቶችን የያዘው ፈተናን ቁጥራቸው 2,843 (ሁለት ሺ ስምንት መቶ አርባ ስድስት) ተማሪዎች ለማስፈተን እቅድ ተይዞ 2,683 ተማሪዎች ፈተናውን እንዲወስዱ ማድረግ ተችሏል፡፡

እንደ ዳይሬክቶሬቱ ዳይሬክተር ዶ/ር ጅብሪል ገለፃ የመውጫ ፈተናውን ለመፈተን በድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ በኩል በ38 የትምህርት አይነቶች  ከተመዘገቡት 1,810 ተማሪዎች ውስጥ 1,791 ተማሪዎች የመውጫ ፈተናውን ሲወስዱ 19 ተማሪዎች ፈተናውን ሳይወስዱ ቀርተዋል፡፡ ተማሪዎቹ ፈተናውን መውስድ ያልቻሉት ፈተናውን ለመውሰድ የሚጠይቀውን መስፈርት ማሟላት ባለመቻላቸውና በራሳቸው የግል ምክንያት ነው፡፡፡

በተመሳሳይ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲን የመፈተኛ ጣቢያቸው እንዲሆን የመረጡ፣ የጤና ሚኒስቴር ያስፈተናቸው ተማሪዎች እንዲሁም  ከሪፍትቫሊ ዩኒቨርሲቲ ፣ ከአዲስ አበባ ሜዲካልና ቢዝነስ ኮሌጅ ፣ ከሲቲ ሜዲካልና ቢዝነስ ኮሌጅ እና ከሉሲ ኮሌጅ 1,033 ተማሪዎች ተመዝግበው 892 ተማሪዎች የመውጫ ፈተናውን ሲወስዱ 141 ተማሪዎች ደግሞ ፈተናውን ሳይወስዱ ቀርተዋል፡፡

ከግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ ፈተናውን ካልወሰዱት ተማሪዎች መካከል ከሲቲ ሜዲካልና ቢዝነስ ኮሌጅ የሂዩማን ኒውትሪሽን 55 ተማሪዎች ብልጫውን ይይዛሉ ያሉት ዶ/ር ጅብሪል ኮሌጁ ተማሪዎቹን ባለማዘጋጀቱ ምክንያት ፈተናውን መውሰድ አልቻሉም፡፡ አንድ ተማሪም የሞባይል ስልክ ደብቆ ይዞ ገብቶ በመገኘቱ ከፈተና ውጪ ከመደረጉ በስተቀር ፈተናው በተያዘው መርሀግብር መሠረት ያለምንም ችግር በስኬት ማጠናቀቅ መቻሉን ተናግረዋል፡፡ 

በዚህ መሠረትም የመውጫ ፈተናውን ተመዝግበው ፈተናውን መውሰድ የቻሉ ተማሪዎች በድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ በኩል 98.96 በመቶ ማሳካት ሲቻል በግል የከፍተኛ የትምርት ተቋማት በኩል ደግሞ 86.36 በመቶ ማሳካት መቻሉንም ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው የቅበላና አካዳሚክ ሪከርድ አልሙኒ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ጅብሪል አብዱልቃድር አብራርተዋል፡፡   

በዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶ/ር መገርሳ ቃሲም በበኩላቸው የመውጫ ፈተናው ያለምንም ችግር  በተያዘለት መርሀግብር እንዲሳካ ዩኒቨርሲቲው በቂ ዝግጅት ማድረጉን ገልፀው በተለይም ከመብራት መቆራረጥ ጋር ችግር እንዳይከሰት አውቶማቲክ ጀኔሬተርን በማዘጋጀት የተሰራው ሥራ ስኬተማ እንደነበረ ተናግረዋል፡፡

ዘንድሮ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የትምህርት ሚኒስቴር ለተመራቂ ተማሪዎች አዘጋጅቶት የነበረው የመውጫ ፈተና በከፍተኛ የትምህርት ተቋም የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ከሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች አንዱ መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር መገርሳ ዛሬ ያለምንም ችግር በዩኒቨርሲቲያችን በስኬት ለማጠናቀቅ ለቻልነው የፈተና መርሀግብር ትልቅ ድርሻ ለነበራቸው የዩኒቨርሲቲው የትምህርት አመራሮች ፣ መምህራን ፣ የአስተዳደር ሠራተኞች፣ የግቢ ፀጥታና ደህንነት አገልግሎት እና  የፌደራል ፖሊስ አባላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡


Share This News

Comment