Logo
News Photo

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ከድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ጋር በመተባበር ለ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ተፈታኝ ተማሪዎች የሥነ-ልቦና ዝግጅነት ዙርያ ስልጠና ሰጠ፡፡

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲና የድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ በጋራ ባዘጋጁት የስልጠና መድረክ ላይ በአስተዳደሩ ውስጥ ከሚገኙ የመንግስትና የግል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለተወጣጡ  ተማሪዎች በ2015 ዓ.ም ለሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ለሚወስዱ ተማሪዎች የስነ ልቦና ዝግጅት ላይ ያተኮረ ስልጠና ተሰጥቷል።  

በመድረኩ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ  ኃላፊ የሆኑት ወ/ሮ ሙሉካ መሀመድ ሲሆኑ በንግግራቸውም በየትኛውም ነገር ውጤታማ የሚኮነው በተለያዩ ፈተናና ውጣ ውረድ ሲታለፍ መሆኑን ጠቅሰው በዚህ ረገድ የሚገኝ ውጤት ምን ያክል አስደሳችና ጣፋጭ እንደሆነ ተናግረዋል። በመሆኑም ይህ ስልጠና በሥነ-ልቦና ረገድ ተፈታኝ ተማሪዎች ተገቢውን ዝግጅት በማድረግ  ተገቢውን  ውጤት  እንዲያመጡ ለማድረግ መዘጋጀቱን ገልፀዋል። 

በመጨረሻም ወ/ሮ ሙሉካ ከዚህ ስልጠና በኋላ ተማሪዎች በቂ የስነ -ልቦና እና የጥናት ዝግጅት በማድረግ የትምህርት ቤታቸውን  ስም እና የከተማችንን ስም በጥሩ ውጤት ማስጠራት እንደሚገባቸው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ 

በዚህ የስልጠና መድረክ ላይ  የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም የህይወት ተሞክሯቸውን ለተማሪዎች ያካፈሉ ሲሆን ተማሪዎች በህይወታቸው ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መገኘታቸውን ገልጸው ከቀናት በኋላ በሚሰጠው ሀገር አቀፍ ፈተና ላይ  ለተሻለ ውጤት የምትዘጋጁበት ጊዜ ላይ በስነ ልቦና ረገድ ዝግጁ በመሆን ከፈተና ከሚያስተጓጉሉ አላስፈላጊ ነገሮች ተቆጥበው በራስ መተማመን መንፈስ ፈተናውን እንዲወስዱ ምክራቸውን ለግሰዋል። 

በመድረኩ ላይ በፈተና ውጤታማ ለመሆን ስለሚያስፈልጉ የስነ-ልቦና ዝግጁነቶችና ከፈተና ጋር ተያይዞ ስለሚያጋጥሙ ችግሮችና መፍትሄዎቻቸው ዙርያ ስልጠና የተሰጠ ሲሆን ስልጠናውንም የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ልቦና ትምህርት ክፍል መምህራን የሆኑት ረ/ፕ ዝናቤ ስዩም እና ረ/ፕ ወንዱ ተሾመ ሰጥተዋል።  

በመጨረሻም ተማሪዎች ለፈተና ወደተመደቡባቸው ዩኒቨርሲቲዎች በሚሄዱበት ጊዜ ይዘው መሄድ ስለሚፈቀድላቸውና ማድረግ ስላለባቸው ጥንቃቄዎች በዩኒቨርሲቲው አለም አቀፍና ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደቻሳ ጋንፉሬ አማካኝነት ገለፃ ተደርጎላቸዋል። በዚህ ስልጠና ላይ ቁጥራቸው ከ3ሺህ ባለይ የሚሆኑ ተፈታኝ ተማሪዎች ተሳትፈዋል።

Share This News

Comment