Logo
News Photo

የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ለ15ተኛ ጊዜ በተለያዩ የትምህርት መስኮች በቅድመ ምረቃና በድህረ ምረቃ ሲያስተምራቸው የቆዩትን ተማሪዎቹን አስመረቀ።

ዛሬ የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ለ15ተኛ ጊዜ በተለያዩ የትምህርት መስኮች በቅድመ ምረቃና በድህረ ምረቃ ሲያስተምራቸው የቆዩ 1ሺህ 2 መቶ 11 ተማሪዎችን ባስመረቀበት ስነ-ስርዓት ላይ  ዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም  እንደተናገሩት ዩኒቨርስቲው የአፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲነቱን ለማረጋገጥ የተቀናጀ ስራ እየሰራ ይገኛል።

በዘንድሮ ዓመት ችግር ፈቺ የሆኑ 37 የምርምር ስራዎችን በማከናወን  የአካባቢውን ማኅበረሰብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለማቃለል የተለያዩ ጥረቶች በማደረግ ላይ መሆኑን እና ገበያው የሚፈልገውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ከማፍራት አንፃርም ሰፊ  እንቅስቃሴዎች እያደረገ ነው ያሉት ዶ/ር ኡባህ በአሁን ሰዓት ከ15ሺ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ ሲሆን ለአካባቢው ማህበረሰብ 74 ልጆች የመጀመሪያና የሁለተኛ ዲግሪ ነፃ የትምህርት እድል  በመስጠትም ፍትሃዊነት እንዲረጋገጥ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ለመምህራን በውጭና በአገር ውስጥ የትምህርት ደረጃ እንዲያሻሽሉ ከማድረግ በዘለል የተግባር ላይ አጫጭር ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

ተመራቂዎች በቀሰሙት ዕውቀትና ክህሎት ስራ ፈጣሪ በመሆን እንደ አገር የተጀመረውን የልማት ጉዞ ከዳር ለማድረስ ሌት ተቀን መረባረብ እንዳለባቸው  ገለፁት በዚሁ የምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የድሬደዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የንግድ ኢንደስትሪ ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ የተከበሩ አቶ  ሀርቢ ቡህ ናቸው፡፡

መንግስት በትምህርት ተደራሽነት ያስመዘገበውን ውጤት በትምህርት ጥራት ለመድገም በጥናት ላይ የተመሠረቱ የተቀናጁ ስራዎች እያከናወነ ይገኛል ያሉት ም/ከንቲባ ሀርቢ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዘንድሮ የተጀመረው የመውጫ ፈተና እና አምና የ12ተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በዩኒቨርስቲዎች መሰጠት መጀመሩ የዚሁ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

እነዚህን ስራዎች ከማጠናከር ጎን ለጎን ከየዩኒቨርሲቲዎች የሚመረቁ ተመራቂዎች በቀሰሙት ዕውቀትና ክህሎት በመጠቀም የተጀመረውን ከደህነትና ከኋላቀርንት  ለመውጣት በሚደረገው ርብርብ ውስጥ ተግተው መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ዩኒቨርሲቲው አስተዳደሩ የጀመረውን ፈጣን የልማትና የእድገት ጉዞ ከዳር መድረስ እንዲችል የጀመረውን ድጋፍና እገዛ ከቀድሞው በበለጠ አጠናክሮ ይቀትል ዘንድ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

በዚሁ የምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ  ለኢትዮጵያና ለህዝቧ በዓለም አደባባይ፤ በአፍሪካና በአገር ደረጃ ላመጡት ዲፕሎማሲያዊ ውጤቶች፣ ለአገራችን ዘላቂ ሰላምና ልማት መረጋገጥ ታላቅ ጀብዱ አከናውነዋል ላሏቸው ለኢትዮጵያ ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮምሽነር አምባሳደር መሐሙድ ድሪር የክብር ዶክትሬት አበርክቷል።

አምባሳደር መሐሙድ ድሪርም በዚሁ የምርቃት ፕሮግራም ላይ ተገኝተው ለተሰጣቸው የክብር ዶክትሬት የዩኒቨርሲቲውን ማህበረሰብ አመስግነው ለተመራቂዎች የስራ መመሪያ ሰጥተዋል።

በመጨረሻም ከተመራቂዎቹ መካከል በትምህርታቸው የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተመራቂዎች የዋንጫ፣ የሜዳሊያ እና የምስክር ወረቀት እንዲሁም ከዳሽን ባንክ ድሬደዋ ዲስትሪክት የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

Share This News

Comment