Logo
News Photo

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያስለጠናቸውን 3,559 ተማሪዎችን አስመርቋል፡፡

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ለ13ኛ ጊዜ በመጀመሪያ እና በሁለተኛ ድግሪ የትምህርት መስኮች ያስተማራቸውን 3,559 (ሶስት ሺ አምስት መቶ ሃምሳ ዘጠኝ) ተማሪዎችን በደማቅና ባማረ ዝግጅት አስመርቋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በወጣትነት ዕድሜ ውስጥ ከ22 ሺህ በላይ ምሩቃንን በማስመረቅ ሀገራዊውን ተልዕኮ በማፍራት የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ የሚገኝ የከፍተኛ የትምህርት ተቋም ነው፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ኡባህ አደም ለተመራቂ ተማሪዎች ባደረጉት ንግግር አገራችን የሚትፈልገውን የሰለጠነ የሰው ሀይል በጥራት ከማቅረብ በተጨማሪ ማህበራዊ ዕድገት ማረጋገጥ የሚያስችሉ ችግር ፈቺ ምርምር ማከናወንና የአከባቢውን ማህበረሰብ ባሳተፈ መልኩ የተለያዩ አገልግሎቶችን መስጠት የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ስራዎች እያከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር ኡባህ አደም አያይዘው ዩኒቨርሲቲው የአኘላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ መሆኑን አንስተው ተቋማዊ መዋቅር እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በዛሬው ዕለት ከተመረቁት 3,559 (ሶስት ሺ አምስት መቶ ሃምሳ ዘጠኝ) ተመራቂ ተማሪዎች መካከል 22 የሚሆኑ የውጪ ሀገር ተማሪዎች እንደሆኑና ዩኒቨርሲቲው አዳዲስ ስርዓተ ትምህርት ቀርጾ እየሰራ እንደሚገኝና 128 (ምት ሀያ ስምንት) የምርምር ስራዎች እየተከናወነ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
የዕለቱ የክብር እንግዳና የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሰቢና በሚኒሲቴር ማዕረግ የዴሞክራሲ ግንባታ ማዕከል ኃላፊ ክብር አቶ ዛዲግ አብርሃ ለተመራቂ ተማሪዎች በብዙ ውጣ ውረዶች አልፋችሁ ለዛሬው ዕለት በመድረሳችሁ እንኳን ደስ አላችሁ በማለት ለተመራቂዎች የስራ መመሪያ ሰጥተዋል። አቶ ዛዲግ አያይዘው የዛሬ ተመራቂዎች አገራቸውን በቁጭትና በወኔ እንዲያገለግሉ እና ለአገራችን ሰላም የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡ በተጨማሪም ሀገሬ ከእኔ ምን ትፈልጋለች ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል በማለት በኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንድ ይህ ጦርነት በአሸናፊነት እንደሚጠናቀቅ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡ ዜጎቿ ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ አሳስበው የዛሬ ተመራቂዎች ሀገር የማደን ስራ መስራት ይኖርባችኋል ብለዋል። በመጨረሻም የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲን የምስሯቋ የልህቀት ማዕከል ለማድረግ እንደሚሰሩና የመምህራኖቻችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ ከድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ምላሽ እየተገኘ መሆኑንም በንግግራቸው አንስቷል፡፡
አቶ ከድር ጁሃር የድሬዳዋ ከተማ ከንቲባና የዩኒቨርሲቲው ቦርድ ም/ሰብሳቢ በበኩላቸው በዛሬው ቀን ትምህርታችን በትጋትና በፅናት ተከታትላችሁ ለዚህ በመብቃታችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል:: አቶ ከዲር አያይዘው ሀገራችን ከውስጥም ከውጪም የተነሱባት ጠላቶቿን ለአንደና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ ከሀገር መከላከያና ከፀጥታ ሀይሉ ጋር በመሆን ሰራቸውን ከንቱ ለማድረግ በትጋት መስራትና አከባቢያችሁንና አገራችሁን መጠበቅ እንዳለባቸው እንዲሁም በምትሄዱበት ቦታ ሁሉ ለአገራቸው ሰላም ዘብ መቆም የምትችሉትን አስተዋጽኦ ማበርከት አለባችሁ በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፋል፡፡
ተማሪ ዳንኤል ጌታቸው የተማሪዎች ህብረት ፕሬዚዳንት ለተመራቂዎቹ ባስተላለፈው መልዕክት ምሩቃን ከብሔርተኝነት አስተሳሰብ በመውጣት ለሀገር እድገት፣ሠላምና በተመረቁበት የሙያ መስክ ውጤታማ ስራ መስራት እንደሚገባቸው አሳስቧል፡፡
በመጨረሻም ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የሜዳሊያና የዋንጫ ሽልማት ከክብር እንግዳው በመቀበል የምረቃው ፕሮግራሙ ተጠናቋል፡፡

Share This News

Comment