Logo
News Photo

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በአሰገደች አረጋዊያን መርጃ ማዕከል ለሚኖሩ አረጋዊያን የተኝቶ ህክምና መከታተያ ክሊኒክ አስገንብቶ ዛሬ አስመረቀ፡፡

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት በዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማኅበረሰብ አቀፍ አገልግልት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሰለሞን ዘሪሁን እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማሳተማርና ከጥናትና ምርምር ተልዕኮው ጎን ለጎን በማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት በርካታ ተግባራትን ያከናውናል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በተለይም ለከፋ ችግር ለተጋለጡና ለአቅመ ደካማ ወገኖች ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ ገልጸው በዛሬው እለትም በአሰገደች አረጋዊያን መርጃ መዕከል የተደረገው ድጋፍ የዚሁ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ለማዕከሉ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው  የህክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ሁሴን መሐመድ በበኩላቸው ለአረጋዊያኑ የተኝቶ ህክምና አገልግሎት የሚያገኙበት ክሊኒክ የተገነባው በኮሌጁ ተመራቂ ተማሪዎችና መምህራን ትብብር ነው፡፡

ተማሪዎቹና መምህራኑ ከኪሳቸው ወጪ ባደረጉት ገንዘብና በከተማዋ ከሚገኙ የተለያዩ ግለሰቦችና ድርጅቶች በተሰባሰበ ገንዘብ ግንባታው ለማጠናቀቅ የተቻለ ሲሆን አጠቃላይ የግንባታው ወጪ ከ200 መቶ ሺህ ብር በላይ መሆኑ ተናግረዋል፡፡

የአሰገደች አረጋዊያን መዕከል ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ እመቤት አሸኔ ለተደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን ገልፀው በተለይ የዩኒቨርሲቲው የህክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ሀኪሞች የበጎ ፍቃድ የነፃ የህክምና አገልግልት አሁን ከሚሰጡጥ በበለጠ እንዲሰጡ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

ለማዕከሉ የሚሰጠው ድጋፍ ሰፋ ባለ መልኩ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የገለፁት ዶ/ር ሰለሞን ማዕከሉ ያሉበትን ችግሮች በጥናት በመለየት በቀጣይ ድጋፍና እገዛው ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

በጎፍቃደኛ  ተመራቂ ተማሪዎቹንና መምህራኑን በማስተባበር የግንባታው ሥራ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ ትልቅ ሚና የነበረው በዩኒቨርሲቲው ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህር ይበቃል ማናዬ ክሊኒኩ በቀጣይ አሁን ካለበትም የተሻለ አገልገሎት መስጠት እንዲችል የተጀመረው እንቅስቃሴ የበለጠ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብሏል፡፡

በአሰገደች አረጋዊያን መርጃ ማዕከል ውስጥ ነዋሪ የሆኑት አረጋዊያን በበኩላቸው ከእድሜ መግፋት ጋር ተያይዞ ከቅጥር ግቢው ውጪ በሚወስዱት ህክምና ከፍተኛ እንግልት ይደርስባቸው የነበረ  መሆኑን ጠቅሰው አሁን ግን ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በቅጥር ግቢያቸው ውስጥ ተኝተው መታከም የሚችሉበትን ክሊኒክ ስለገነባለቸው ከዚህ ቀደም ይገጥማቸው የነበረውን መጉላላት እንደሚቀንስላቸው ተናግረው ለዚህም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

በመጨረሻም በአረጋዊያን ማዕከሉ የገቢ ምንጭን ለማሳደግ በከተማ ግብርና የተሰሩ ስራዎች በዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች ጉብኝት የተደረገ ሲሆን ለአረጋዊያኑም የነፃ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ምርመራ ተደርጎላቸዋል፡፡


Share This News

Comment