Logo
News Photo

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በመውጫ ፈተና ላይ ጉልህ አስተዋጾ ለነበራቸው ትምህርት ቤቶች፣ ትምህርት ክፍሎች እና የስራ ክፍሎች እውቅና ሰጠ፡፡

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በእቅድ ይዞ እንቅስቃሴ ከጀመረባቸው ተግባራት መካከል  ለዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎች እንዲሰጥ የተደረገው የመውጫ ፈተና ተጠቃሽ ነው፡፡

በዚህ መሠረትም ባላፈው ሀምሌ ወር ላይ በአገሪቱ በሚገኙ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ተመራቂ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና እንዲወስዱ ተደርጓል፡፡

የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ የመውጫ ፈተናውን በተሳካ መልኩ ማጠናቀቅ እንዲችል ጉልህ አስተዋጾ ለነበራቸው ማለትም ተማሪዎቻቸውን በሞዴል Exam ከማዘጋጀት አንጻር ፣ የመውጫ ፈተናውን ለማከናወን የሚያስፈልጉ ኢንፍራስትራክቸር እና GoBEZ የሞዴል ፈተና ሶፍትዌርን በማዘጋጀት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያበረከቱ የስራ ክፍሎች እና ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ የትምህርት ክፍሎችን በተዘጋጀው ፕሮግራም ላይ እውቅና ተሰጥቷል፡፡

በፕሮግራም ላይ  የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም በመገኘት እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲው በሙሉ ኃላፊነት የመውጫ ፈተናውን ያለምንም ክፍተት ተመራቂ ተማሪዎች የመውጫ ፈተናውን መውሰድ እንዲችሉ ማድረጉን ገልጸው ፈተናው ከመሰጠቱ በፊት ዩኒቨርሲቲው በተቻለ አቅም በቂ ዝግጅት ማድረጉን የጠቆሙት ዶ/ር ኡባህ ለዚህም የትምህርት ክፍሎች እና የሚያስፈልጉ የመፈተኛ ላብራቶሪዎችን በበቂ መሰረተ ልማት በማዘጋጀት የነበራቸው ድርሻ ከፍተኛ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

ዶ/ር ኡባህ አያይዘው በመጀመሪያው የመውጫ ፈተና የተገኙትን ጠንካራ ጎኖች በማስቀጠል ደካማ ጎኖችንም በማሻሻል በ2016 ዓ.ም በሚሰጠው የመውጫ ፈተናን በስኬት ለመወጣትና የመውጫ ፈተና ወስደው የሚያልፉ ተማሪዎችን ከአሁኑ በበለጠ ዝግጅት ለማድረግ ከወዲሁ ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ ከፈተናው በፊት፣ በፈተና ወቅት እና ከፈተና በኋላ የነበሩ ሁኔታዎችን አስመልክተው የትምህርት አመራሮቹና መምህራኑ ሃሳብና አስተያየቶችን ያነሱ ሲሆን በመጨረሻም ለሥራው ስኬት ጉልህ አስተዋጾ ለነበራቸው የምስጋናና የእውቅና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።


Share This News

Comment