Logo
News Photo

በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ ሳምንት ተከበረ

በሀገር አቀፍ ደረጃ የሳይንስ ሳምንት ከህዳር 6 እስከ ህዳር 14 በተለያዩ ዝግጅቶች የሚከበር ሲሆን ይህንን በአል በማስመልከት በዛሬው  እለት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ሴሚናር አካሂዷል።


ሴሚናሩን በንግግር የከፈቱት የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር መገርሳ ቃሲም ሲሆኑ በንግግራቸውም ሳይንስ ለአንድ ሃገር እድገትና ልማት ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ት/ቤቶች በትብብር በመስራት በሳይንስና ፈጠራ እውቀት እና ክህሎት ያላቸው ተማሪዎችን ወደ ዩኒቨርሲቲ እንዲቀላቀሉ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ 


በሴሚናሩ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር  ዶ/ር ወንዲፍራው ደጀኔ ሲሆኑ በንግግራቸውም በመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ያሉ ተማሪዎች ለሳይንስ ትምህርት ዓይነቶች ያላቸውን አሉታዊ አመለካከት በመቀየር እና  የሳይንስ ፍቅር እንዲያድርባቸው ለማድረግ የሳይንስ ሳምንት በየአመቱ መከበሩ ሚናው የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል። 


በተጨማሪም ዶ/ር ወንዲፍራው  በሳይንስና ቴክኖሎጂ የተሻለ እውቅትና ክህሎት ያላቸው ተማሪዎችን  ከት/ቤቶች ጋር በጋራ በመለየት የተሻለ ነገር እንዲፈጥሩ ለማስቻል የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት የሳይንስ  መምህራንን እውቀትና የማስተማር ክህሎታቸውን የሚያሻሽሉ ተከታታይ ስልጠናዎችን ዩኒቨርሲቲው እየሰጠ እንደሆነና የሳይንስ ዝንባሌና የፈጠራ ችሎታ ያላቸውን ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው በተቋቋመው የሳ.ቴ.ም.ሂ (STEM) ማእከል በማስተማር ላይ እንደሚገኙም ጨምረው ተናግረዋል፡፡ 


በዚህ ሴሚናር ላይ መምህራን የተማሪዎቻቸውን የሳይንስ ግንዛቤና የፈጠራ ክህሎት እንዴት በእለት-ተለት ህይወታችን የምንተገብራቸውን ነገሮች በመጠቀም በቀላሉ ማሳደግ እንደሚችሉና ሳይንስን አርቲስቲክ በሆነ መልኩ ማስተማር እንዲሚቻል የሚጠቁሙ ሶስት ፅሁፎች በዩኒቨርሲቲው መምህራን ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን በሴሚናሩ ላይም በድሬዳዋ አስተዳደር የሚገኙ ከመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተጋበዙ የሳይንስ ትምህርት መምህራን እና የዩኒቨርሲቲው መምህራን ተሳትፈውበታል።  


Share This News

Comment