Logo
News Photo

የተማሪዎች የአደንዛዥ እጽና የአደጋ ተጋላጭነት ..............

በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የሴቶና ወጣቶች፤ ኤች.አይቪ ኤድስ እና ልዩ ፍላጎት ዳይሬክቶሬት ከድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ጋር በመተባበር የተማሪዎችን የአደንዛዥ እጽና የአደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስ የውይይት መድረክ አዘጋጅቷል፡፡


በዚሁ መድረክ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ተወካይ እና የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝደንት የሆኑት ዶ/ር መገርሳ ቃሲም እንደገለጹት በአሀኑ ሰዓት  በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የተማሪዎች የአደንዛዝ እጽንና የአደጋ ተጋላጭነትን ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን በቅርቡ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት መታወቁን ገልጸዋል፡፡


ዶ/ር መገርሳ አክለውም ይህንን አሳሳቢ ችግር ለመቅረፍም ዩኒቨርሲቲው ከድሬደዋ ከተማ አስተዳደር  ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ እና ከተለያዩ ባለድርሻ  አካላት ጋር እንቅስቃሴ እያደረገ ቢሆንም ችግሩን ትርጉም ባለው መልኩ መቅረፍ እንዲቻል ግን አብዛኛው ተማሪዎች አዘውትረው በሚውሉበት ነዋሪ የሆነው የዩኒቨርሲቲው አካባቢ ማህበረሰብ ትልቁን ሚና ሊጫወት ይገባል ብለዋል፡፡    

የዛሬው የውይይት መድረክም ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ የተዘጋጀ መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር መገርሳ የተማሪዎችን የአደንዛዥ እፅና የተለያዩ አደጋዎች ተጋላጭነት በመቀነስ ተማሪዎች በትምህርታቸው  ውጤታማ በመሆን የሀገር ተረካቢና ስኬታማ እንዲሆኑ የሁላችንም ርብርብ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡


የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ፈጡም ሙስጠፋ በዚሁ መድረክ ላይ ተገኝተው ባስተላለፋት ምልዕክት በከተማችን ድሬዳዋ የአደንዛዥ እፅ ተጠቃሚዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን ገልፀው የአደንዛ እጽ ተጠቃሚዎች መካከልም የከፍተኛና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ቁጠር ቀላል የማይባል ድረሻ መያዙን ተናግረዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ለችግሩ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ ከቢሮዋቸው ጋር የጀመረውን እንቅስቃሴ እንዲሳካ ቢሮው የበኩሉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡


የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሰለሞን ዘሪሁን በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ችግሩን በጥናት ከመለየት ጎን ለጎን በአደንዛዥ እፅ ሳቢያ ለድብርትና ለአዕምሮ ህመም የሚዳረጉ ተማሪዎች የህክምና እርዳታ የሚያገኙበት የማገገሚያ ማዕከል ዩኒቨርሲቲው ለመክፈት እቅድ እንዳለው ተናግረዋል፡፡


ለአንድ ቀን በቆየው የውይይት መድረክ ላይ የተማሪዎች ማህበራዊና ስነ-ልቦናዊ ችግሮች፣ አደንዛዥ እጽ ስርጭት እና እያስከተለ ያለው ጉዳት በሚል በዩኒቨርሲቲው የሴቶች፣ ወጣቶች እች አይ ቪ ኤድስ እና ልዩ ፍላጎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ተወካይ በሆኑት በወ/ሪት ሃረግ ተክሉ እና የድሬዳዋ ፓሊስ ምክትል ኮምሽነር ማኦ ተሾመ ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

 

Share This News

Comment