Logo
News Photo

የተማሪዎች የሰላም ውይይት መድረክ የማጠቃለያ ፕሮግራም ተካሄደ::

በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ የሕግ ትምህርት ቤቶች ማኅበር ጋር በመተባበር ሲካሄድ የነበረው የተማሪዎች የሰላም ውይይት መድረክ ተጠናቋል፡፡ 

በዚሁ የማጠቃለያ ፕሮግራም ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የህግ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ሮባ ጴጥሮስ ተማሪዎች ሰላም ያለውን ትልቅ ዋጋ ተገንዝበው በአገራችን ዘለቂና አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ውስጥ የራሳቸውን አስተዋፆኦ ማበርክት ይጠበቅባአቸዋል፡፡

በተለይም ሰላማዊ ውይይትን አስመልክት በተከታታይነት ሲወስዱት በነበረው ስልጠናና ትምህርት ልዩነቶችንና አለመግባባቶችን እንዴት መፍታት እንደሚቻል በምክክር ዲሞክራሲያዊ ባህልን ከማሳደግ አንፃር የሚኖረውን የጎላ ፋይዳ ግንዛቤ እንዲያገኙ እድል የሚፈጥርላቸው ነው ብለዋል፡፡

ተማሪዎች ልዩነቶችንና አለመግባበቶችን በንግግርና በውይይት ብቻ የመፍታት ባህል በማዳበር ለሌሎችም በማካፈል የሚጠበቅባቸውን አገራዊ ኃላፊነት ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕግ ትምህርት ቤቶች ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ደርሶልኝ የኔአባት በበኩላቸው ማህበሩ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ከሚገኙ 39 የሕግ ትምህርት ቤቶች ጋር በአሁኑ ሰዓት በመስራት ላይ መሆኑን ጠቅሰው ማኅበሩ በተለይም በሰላም ግንባታና ግጭት አፈታት ዘዴ፣ ጾታ ተኮር ጥቃቶችን ማስቀረትና ህጋዊ ማዕቀፍ ማዘጋጀት እና መሰል ጉዳዮች ላይ ትኩረት እድርጎ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡

በዚህም በአገሪቱ ውስጥ የተሻለ የህግ ትምህርት ስርዓት፣ የተሻለ የህግ የምርምር ስርዓት እንዲኖር እና ውጤታማ ምርምሮች እንዲሰሩ እንዲሁም ነፃ የህግ አገልግልት ድጋፍ እነዲስፋፋ ማድረግ ዋንኛ ዓላማው ማድረጉን አብራርተዋል፡፡

በተመረጡ 8 ዩኒቨርሲቲዎች ላይ በሰላም እሴት ግንባታና ምክክርን አስመልክቶ እየተሰራ ያለው ፕሮጀክት ተጠቃሽ ነው ያሉት አቶ ደርሶልኝ በቀጣይም መሰል ሥራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡

በማጠቃለያ ፕሮግራሙ ላይ አንዳንድ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንደገለፁልን ከሆነ የኢትዮጵያ የሕግ ትምህርት ቤቶች ማኅበር ሲሰጣቸው በነበሩ ስልጠናዎችና የውይይት መድረኮች ልዩነትንና አለመግባባትን እንዴት በሰላማዊ መንግድ መፍታት እንደሚቻል ትልቅ ትምህርት አግንተንበታል ብለዋል፡፡ 

ይህ ደግሞ ትምህርታቸውን ጨርሰው ወደ ማኅበረሰቡ ሲቀላቀሉ ባገኙት እውቀት ከራሳቸው አልፈው ለሌሎችም መጥቀም የሚችሉበትን ሰፊ እድል የሚፈጥርላቸው መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

Share This News

Comment