Logo
News Photo

በድሬዳዋ ዪኒቨርሲቲ የሴቶች እና ወጣቶች ኤች አይ ቪ ኤድስ እና ልዪ ፍላጎት ዳይሬክቶሬት ቢሮ አዘጋጅነት ስለአካል ጉዳተኛ/ስለልዩ ፍላጎት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ።

በዕለቱ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዪኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር መገርሳ ቃሲም ባስተላለፉት መልዕክት የዪኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ስለአካል ጉዳተኛ/ ልዩ ፍላጎት ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ የሴቶች እና ወጣቶች ኤች አይ ቪ ኤድስ እና ልዪ ፍላጎት ዳይሬክቶሬት ቢሮ ስልጠና መዘጋጀቱ የሚበረታታ ነው ብለዋል። አያይዘውም ዪኒቨርሲቲው የአፕላይድ ሳይንስ እንደመሆኑ እና ሀገራችን የአካቶ ትምህርት ስርዓትን ተግባራዊ እንዲደረግ የተጀመረውን እንቅስቃሴ ከመደገፍ አንፃር ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ምቹ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ከጉዳት አልባ ተማሪዎች እኩል ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚገባ ገልፀዋል። 

የዪኒቨርሲቲው የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ተማም አወል በበኩላቸው ለአካል ጉዳተኛ/ልዩ ፍላጎት ተማሪዎች ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር አንጻር የሚሰሩ ህንጻዎችን ጨምሮ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ገልጸው የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች እኩል ተጠቃሚ እና ተፎካካሪ እንዲሆኑ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መዘጋጀቱ ይበል የሚያሰኝ ነው ብለዋል። 


ስልጠናውን በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የግንዛቤ ት/ት እና ንቅናቄ ቡድን መሪ የሆኑት ወ/ሮ አዲስ አሰፋ የሰጡት ሲሆን ‘’እክል እና አካል ጉዳት” በሚል ርዕስ ባቀረቡት ሰነድ ላይ የመብት ጥበቃ ኮንቬንሽን ስለአካል ጉዳትኞች መብት እና ተጠቃሚነት የተቀመጡ ድንጋጌዎችን አቅርበው በተፈጥሮ ይሁን በአደጋ አካል ጉዳት ሊከሰት የሚችል መሆኑን ገልፀዋል። በተጨማሪም ህብረተሰቡ ስለአካል ጉዳተኛ ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ በትብብር መስራት እንደሚገባ አስገንዘበዋል።


በስልጠናው ላይ የአካዳሚክ እና አስተዳደር ሰራተኞች፣ የተማሪዎች ህብረት አመራሮች እንዲሁም አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የተሳተፉ ሲሆን በቀረበው ሰነድ ላይ አስተያየት እና ጥያቄዎችን አቅርበው በቀጣይ መሰራት ስላለባቸው ተግባራት ተወያይተዋል። የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች በበኩላቸው ስለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ያለውን ግንዛቤ ለማሻሻል ስልጠና መዘጋጀቱ መልካም አጋጣሚ እንደሆነ ገልፀው ከጉዳት አልባ ተማሪዎች እኩል ተጠቃሚ እና ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችል ስራ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ እንዲሁም መሰል ስልጠናዎች እና የውይይት መድረኮች ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።


የተማሪዎች ህብረት ፕሬዝዳንት ተማሪ መሃመድ አብደላ በመልዕክቱ ስለአካል ጉዳተኛ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናው ጥሩ ግንዛቤ የፈጠረላቸው መሆኑን በመግለጽ በህብረቱ ውስጥም የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የራሳቸው ተወካይ እንዲኖራቸው ከማድረግ አንፃር ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 

በመጨረሻም የሴቶች እና ወጣቶች ኤች አይ ቪ ኤድስ እና ልዪ ፍላጎት ዳይሬክቶሬት ቢሮ ተወካይ የሆኑት ወ/ሪት አዜብ በመማር ማስተማር ሂደት ውስጥ ለአካል ጉዳተኛ/ ልዩ ፍላጎት ተማሪዎች ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አንስተው ከዚህ የተሻለ ስራ ለመስራት የሁሉንም ትብብር የሚፈልግ መሆኑን አጽንዖት በመስጠት ለስልጠናው መሳካት ጉልህ ድርሻ ለነበራቸው አስተባባሪዎች እንዲሁም ተሳታፊዎች ምስጋና አቅርበው ስልጠናው ተጠናቋል።

Share This News

Comment