Logo
News Photo

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው የሰራዊት አባላት የምግብና የፅዳት ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገ።

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ባለው ጦርነት ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ከ650,000.00 (ስድስት መቶ ሀምሳ ሺ) ብር በላይ የሆነ የምግብና የጽዳት ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገ።

በድጋፍ ርክክቡ ላይ ዩኒቨርሲቲውን በመወከል ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም እንደገለፁት ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የተደቀነብንን የህልውና ስጋት ለመመከት እየተዋደቀ ለሚገኘው ጥምር የፀጥታ ሃይል ችግሩ ከተፈጠረ ጀምሮ ተከታታይ ድጋፎችን እያደረገ እንዳለ ገልፀው በዛሬው እለት ለሀገር ክብር ሲሉ ለቆሰሉና  በሆስፒታሉ ህክምናቸውን እየተከታተሉ ለሚገኙ የሰራዊት አባላት ያላቸውን ከፍተኛ ክብር ለመግለፅና ጉዳታቸው ጉዳታችን፤ ስቃያቸው ስቃያችን ነው ብለን ልናበረታታቸውና ከጎናቸው መሆናችንን ለመግለፅ ነው የመጣነው ብለዋል፡፡

በድጋፍ ስነ-ስርአቱ ላይ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች የተገኙ ሲሆን 10 ሰንጋዎች፤ 200 ካርቶን የገላ ሳሙና እና 10,000 ሊትር ፈሳሽ ሳሙና ለሆስፒታሉ ተወካይ ያስረከቡ ሲሆን አመራሮቹም ዩኒቨርሲቲውና የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ምንጊዜም ከሰራዊቱ ጎን እንደሚቆሙ አረጋግጠዋል፡፡

ሆስፒታሉን በመወከል ድጋፉን የተረከቡት ኮሎኔል ጌትነት አየነው  ሲሆኑ በንግግራቸውም ላይ ድጋፉ ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ያለውን አጋርነት ያሳየበት መሆኑን ገልፀው ዩኒቨርሲቲው እያደረገላቸው ላለው ድጋፍ በሆስፒታሉ ስም ከፍተኛ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

Share This News

Comment