Logo
News Photo

የፀረ ፆታዊ ጥቃት ቀን በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በፓናል ውይይት ተከበረ፡፡

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ሴቶችና ወጣቶች ፣ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ/ እና ልዩ ፍላጎት ዳይሬክቶሬት በአለም አቀፍ ደረጃ ለ32 ጊዜ በአገራችን ኢትዮጵያ ደግሞ ለ18ኛ ጊዜ እየተከበረ የሚገኘውን የፀረ ፆታዊ ጥቃት (የነጭ ሪቫን ) ቀንን አስመልክቶ የፓናል ውይይት አካሂዷል፡፡


የፓናል ውይይቱን በንግግር የከፈቱት በዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር መገርሳ ቃሲም በሴቶች ላይ የሚፈፀምን ጥቃት መከላከልና ሲፈፀምም አይቶ አለማለፍ የሁላችንም ኃላፊነት ሊሆን ይገባል፡፡

በተለይም ወንዶች በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት በመከላከል ረገድ ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው ያሉት ዶ/ር መገርሳ ችግሩን ትርጉም ባለው መልኩ ከመቅረፍ አኳያም ለጉዳዩ ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡


በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ሴቶችና ወጣቶች ፣ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ/ እና ልዩ ፍላጎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ዝናሽ ደሳለኝ በበኩላቸው በሴቶች ላይ የሚፈፀም ጥቃትን ለማስቀረት በአለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ ሁሌም ከህዳር 15 እስከ ህዳር 30 ለተከታታይ 16 ቀናት በተለያዩ ዝግጅቶች የሚከበር መሆኑን ጠቅሰው የዘንድሮው የፀረ-ፆታዎ ጥቃት (የነጭ ሪቫን) ቀን "መቼም ፣የትም ፣በምንም ሁኔታ ፆታዊ ጥቃትን ዝም አንልም" በሚል መሪ የሚከበር መሆኑን ተናግረዋል፡፡


በፓናል ውይይት ላይ በድሬደዋ አስተዳደር ሴቶችና ህፃናት ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ቡድን መሪ የሆኑት አቶ ፀጋዬ አበጋዝ እና ከድሬዳዋ ፖሊስ ኮምሽን ኮማንደር አየለች ታምሩ የፆታዊ ጥቃትን አስመልክተው የውይይት መነሻ ፅሁፍ አቅርበው በተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎችና አስተያየቶች በማንሳት ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

Share This News

Comment