Logo
News Photo

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በቴክስታየልና ፋሽን ዲዛይን ትምህርት ቤት መምህራንና ተማሪዎች የተዘጋጀው ሁለተኛው ዙር ዓመታዊ የአልባሳት ፋሽን ትዕይንት በዩኒቨርሲቲው መግቢያ ዋናው በር በደማቅ ሁኔታ ተከናወነ፡፡

ፕሮግራሙን በማስመልከት በማስጀመሪያ መርሀ-ግበሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የትምህርት ቤቱ ዲን አቶ አስናቀ ከተማ የቴክስታየል ምህንድስና እና የፋሽን ዲዛይን መምህራንና ተማሪዎች በትምህርት ቤቱ የሚገኙ ቤተ-ሙከራዎችንና ወርክሾፖችን በመጠቀም በንድፈ-ሀሳብ የተማሯቸውን ነገሮች ወደ ተግባር በመቀየር የቀረቡ ስራዎች መሆኑን በመግለፅ በቀጣይ ተመሳሳይ ተግባር ተኮር ስራዎችን ለማቅረብ እየሰሩ መሆኑን ገልፀዋል፡፡


የኢንስቲትዩቱ ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ገደፋዪ መንግስት ለጨርቃጨርቅ ዘርፉ የሰጠውን ትኩረትና የድሬዳዋ አስተዳደር የኢንዱስትሪ መዳረሻነትን ከግምት ውስጥ በማስገባት በዘርፉ ገበያው የሚፈልጋቸውን ምሩቃን ለማፍራት በትምህርት ቤቱ በተግባር የተደገፈ የመማር ማስተማር ስራዎች ለማከናወን የሚረዱ ግብዓቶችን በማሟላት ይህን መሰል ትዕይንት ለማዘጋጀት መቻሉን በመጥቀስ፤ በፕሮግራሙ ላይ ለመታደም ለተገኙ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡


በመቀጠልም የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም ዩኒቨርሲቲያችን በሀገራችን ከሚገኙ አስራ አምስት የአፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱ መሆኑን በመጥቀስ በኢንጅነሪንግ፣ ቴክኖሎጂ፣ በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ እንዲሁም በጤና ዘርፎችን የትኩረት መስክ በማድረግ እየሰራ መሆኑን በማስታወስ ይህ ፕሮግራም ተማሪዎች ተግባር ተኮር እውቀትን ይዘው ወደ ኢንዱስትሪው እንዲቀላቀሉ እና የቀሰሙትን እውቀት መሰረት በማድረግ ስራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ለማደረግ ያለመ መሆኑን በመጥቀስ ሌሎች ትምህርት ቤቶችም ይህን ተሞክሮ በመውሰድ በቀጣይ የተማሪዎችንና የመምህራንን ስራዎች ለባለድርሻ አካላት ለማስተዋወቅ መስራት እንዳለባቸው በመግለፅ፤ የፕሮግራሙን አዘጋጆችንና ትምህርት ቤቱን በማመስገን ፕሮግራሙን በይፋ አስጀምረዋል፡፡


በመምህራንና ተማሪዎች የተዘጋጁ ስራዎች በአስራ አንድ ምድብ ተከፍለው ለታዳሚው የቀረቡ ሲሆን በመጨረሻም ፕሮግራሙን በተለያዩ ደረጃዎች ስፖንሰር ያደረጉ ኤምኤም ሆቴልና ንጉስ ከአልኮል ነፃ መጠጥን እንዲሁም ለተጋባዥ ባለድርሻ አካላት የእውቅና ምስክር ወረቀት በእለቱ የክብር እንግዳ የድሬዳዋ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ ሳሊም ኡስማን ተበርክቷል፡፡

Share This News

Comment