Logo
News Photo

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታል በዛሬው እለት ተመርቆ በከፊል ለአገልግሎት ክፍት ሆነ፡፡

በ2000 ዓ.ም ላይ ግንባታው የተጀመረው የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታል መሀል ላይ በተፈጠሩ የተለያዩ ችግሮች ሳቢያ ግንባታው ሳይጠናቀቅ ከ16 ዓመት በላይ ፈጅቷል ፡፡

ሆስፒታሉን በ2011 ዓ.ም ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በባለቤትነት ተረክቦት ቀሪ ግንባታዎችን አጠናቆና አስፈላጊ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ስራዎችን በማከናወን በዛሬው እለት በይፋ ተመርቆ ለአገልግልት ክፍት እንዲሆን አድርጓል፡፡


በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የጤና ሚኒስቴር ሚንስትር ዲዔታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ ድሬዳዋ የምስራቁ የሀገራችን ክፍል የንግድ ፣ የኢንዱስትሪ ማዕከል እንደመሆኗ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከከተማዋ እድጋጅገት ጋር የሚመጥን የጤና ተቋም ሊኖራት ግድ ይላል ብለዋል፡፡

በዚህ ረገድም የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታል ከሚገኝበት አካባቢው አልፎ እንደ ሀገርም በጤናው ዘርፍ ትልቅ አስተዋፅዖ መወጣት የሚችል ተቋም ሆኖ የተቋቋመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሆስፒታሉ በድሬዳዋ ከሚገኙ አጠቃላይ ሆስፒታሎች እና በሶማሌና በኦሮምያ ክልል ከሚገኙ የጤና ተቋማት በመቀናጀት በሽታን አስቀድሞ በመከላከሉ እንቅስቃሴ ላይ የራሱን የሆነ አሻራ ማሳረፍ እንደሚኖርበት ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ ተናግረዋል፡፡


በዚሁ የምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ክቡር አቶ ከድር ጁሀር በበኩላቸው የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታል ከአስተዳደሩ ባለፈ ለአጎራባች ክልሎችና የጎረቤት አገር ህዝቦች የጤና አገልግሎት ሽፋንን የሚያሳድግ ነው፡፡

ሆስፒታሉ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በዩኒቨርሲቲው ስር ሆኖ አገልግሎት እንዲሰጥ መደረጉ በጤናው ዘርፍ የሚደረጉ የጥናትና የምርምር ሥራዎችን በብዛትም ሆነ በጥራት በመጨመር በሽታን አስቀድሞ በመከላከል ጤናው የተጠበቀና ኢንደስትሪው የሚፈልገውን አምራች ዜጋን በማፍራት ሀገራችን የጀመረችውን የተፋጠነ የልማት ጉዞ ከዳር በማድረስ እድግት እንዲመዘገብ የማድረግ አቅም ያለው ነው ብለዋል፡፡

በዚህ ረገድ የማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታሉ የጤና አገልግሎት ለድሬዳዋና ለአካባቢዋ ነዋሪ መስጠት መጀመሩ የሚኖረው ፋይዳ ዘርፈ ብዙና በህዝባችን ህይወት ላይ የሚፈጥረው በጎ ተፅዕኖ ጎልቶ የሚታይ በመሆኑ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ ያደርጋል ብለዋል፡፡


በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ በመገኘት የስነ-ስርዓቱን ታዳሚዎች እንኳን ደህና መጣችሁ ያሉት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም በበኩለቸው ዩኒቨርሲቲው የማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታሉን በ2011 ዓ.ም ተረክቦ በ500 ሚሊዮን ብር ቀሪ ሥረዎችን አጠናቆ ለምረቃ የበቃና በከፊል ሥራ ማስጀመር የተቻለ መሆኑን ጠቁመው በአሁኑ ሰዓትም ሆስፒታሉ ህሙማን ተኝተው መታከም የሚችሉባቸው 400 አልጋዎችን የያዘ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


በከፊል ሥራ የጀመረውን የማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታሉን ቀሪ ሥራዎችን አጠናቆ በሙሉ አቅሙ አገልግሎት በመስጠት የህብረተሰቡን የጤና አገልግሎት ሽፋን የጥራት ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ተደራሽ ለማድረግ በየአቅጣጫው የተጀመሩ ርብርቦች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል፡፡

በዚህ ረገድም ሁሉም ወገን ይሄን ከሀገር አልፎ ለጎረቤት አገራት ህዝቦች ሳይቀር ጥራት ያለው ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ዘመናዊና ግዙፍ ሆስፒታል በሙሉ አቅሙ አገልግልት መስጠት እንዲችል ሁሉም ሰብአዊ ግዴታውን ሊወጣ ይገባል ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡


የድሬደዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ፅጌረዳ ክፍሌ በበኩላቸው የማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታሉ በይፋ ተመርቆ በከፊል ሥራ መጀመሩ በድሬዳዋ በሚገኙ የጤና ተቋማት ላይ የተፈጠረውን መጨናነቅ በመቀነስ የነዋሪው የጤና አገልግሎት ሽፋን ያሳድጋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ቢሮው ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመተባበር ሆስፒታሉ በሙሉ አቅሙ አገልግልት መስጠት እንዲችል የማድረጉን ሥራም በቻለው አቅም ሁሉ እገዛና ድጋፍ በማድረግ የበኩሉን መወጣቱን ይቀጥላል ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡ 


በምረቃው ስነ-ስርዓቱ የተገኙ እንዳንድ የድሬዳዋ ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት ይሄ ግዙፍና ዘመናዊ ሪፈራል ሆስፒታል ቤታችን ደጃፍ ላይ ግንባታው ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት መሆኑ በቀጣዩ ዘመን ከበሽታ የተጠበቀን አካባቢን ከመፍጠር አንፃር ትልቅ ተስፋን የሚያጎናፅፍ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

Share This News

Comment