Logo
News Photo

ጤና ለሁለንተናዊ ለውጥና እድግት ግብዓትና ግብ መሆኑን በመረዳት በጤናው ዘርፍ ላይ የሚሰማሩ ባለሞያዎች ኃላፊነታቸውን በከፍተኛ ሀገራዊ ስሜትና ብቃት መወጣት ይኖርባቸዋል ሲሉ የጤና ሚኒስትር ሚኒስቴር ዲዔታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ አስገነዘቡ፡፡

ሚኒስትሩ የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ በዛሬው እለት በህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጁ ለ7ኛ ዙር እንዲሁም በማኅበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ እንዲሁም በቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ተማሪዎችን ባስመረቀበት ስነ-ስርዓት ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ሀገራችን ወደ ብልፅግናው ማማ ላይ የምታደርገውን ግስጋሴ ለማሳካት ጤና ለሁሉም እንቅስቃሴያችን መሠረት ነው፡፡

"ጤና ለሁለንተናዊ ለውጥ መምጣት ግብዓትና ግብ ነው" ያሉት ሚኒስትር ዲዔታው ዶ/ር ደረጀ በጤናው ዘርፍ የምናደርገውን ኢንቨስትመንት እያጠናከርን ወደ ምንመኘው እድገት ላይ መድረስ ይጠበቅብናል፡፡

በዚህ ረገድም በዘርፉ የሚሰማሩ ባለሞያዎች የማይተካ ሚና አላቸው ያሉት ሚኒስትር ዲዔታው በጤናው ዘርፍ ላይ የሚሠማሩ ባለሞያዎች የተጣለባቸውን ኃላፉነት በትልቅ ሀገራዊ ስሜትና በብቃት መወጣት ይኖርባቸዋል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡


በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በጤናው ዘርፍ የሚፈለገው እድግት እንዲመዘገብ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች በመደረግ ላይ መሆናቸውንና በዚህም የተለያዩ ለውጦችን መመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በተለይም በጤናው ዘርፍ ብቁና የሠለጠነ የሰው ኃይል ከማፍራት አንፃር ዩኒቨርሲቲው በጤና ሳይንስ ኮሌጁ በተለያዩ የትምህርት ክፍሎች ተማሪዎችን እያስተማረ የሚያስምርቅ መሆኑን ጠቅሰው እነዚህ ተማሪዎች ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ሥራ ሲሰማሩ ህብረተሰቡን መልካም  ስነ-ምግባርን በተላበሰና የጥራት ደረጃውን በጠበቀ መልኩ አገልግልት መስጠት እንዲችሉ በተግባር የተደገፉ የተለያዩ ስራዎች የሚከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

እንደ ዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ ገለፃ በዘንድሮ ዓመት በዩኒቨርሲቲው በህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የመውጫ ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች 98.7 በመቶ ተማሪዎች ፈተናውን ማለፍ መቻላቸው ለዘርፉ የተሰጠውን ከፍተኛ ትኩረት ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

እነዚህ የተገኙ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች በማስቀጠል በጤናው ዘርፍ ብቁና የሰለጠነ ባለሞያዎችን በብዛትና በጥራት በማፍራት መከላከል ላይ ትኩረት ያደረገው የጤና ፖሊሲያችን እንዲሳካ ዩኒቨርሲቲው የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡ 


በዚሁ የምርቃ ስነ-ስርኣት ላይ የድሬዳዋ አስተዳደር አፈ-ጉባዔ ክብርት ወ/ሮ ፈቲሃ አደን ፣ም/አፈጉባዔ ክብርት ወ/ሮ ከሪማ አሊ ፣የድሬደዋ አስተዳደር የጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ፅጌረዳ ክፍሌ እና የተለያዩ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንዲሁም የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል፡፡

Share This News

Comment