Logo
News Photo

የአካል ጉዳተኞች ቀን በድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ተከበረ፡፡

በአለም አቀፍ ደረጃ ለ30ኛ ጊዜ በሃገራችን ደግሞ ለ29ኛ ጊዜ" የአካል ጉዳተኞች መሪነትና ተሳትፎ ለማረጋገጥ አካታች፣ ተደራሽነት እና ዘላቂ ድህረ ኮቪድ 19 አለምን እንገንባ" በሚል መሪ ቃል  የሚከበረውን የአካል ጉዳተኞች ቀን ምክንያት በማድረግ በድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ ተማሪዎች እና የአስተዳደር ሠራተኞች የተካፈሉበት የውይይት መድረክ ተዘጋጅቷል፡፡

በመድረኩ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም እንደገለጹት እንደ የአለም የጤና ድርጅትና እንደ አለም ባንክ መረጃ መሠረት በአሁኑ ሰዓት ከአጠቃላይ የሃገራችን ህዝብ ውስጥ 17 በመቶ የሚሆነውን ቁጥር የሚሸፍኑት አካልጉዳተኛ ዜጎች መሆናቸውን አንስተው በሃገራችንም ሆነ ድሬደዋ ከተማ የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት ከማሳደግ አንፃር ያሉትን ክፍተቶች በመድፈን ሰፊ ስራ ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡ 

ዩኒቨርሲቲያችን ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ተደራሽ ለማድረግ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ ነው" ያሉት ዶ/ር ኡባህ በዩኒቨርሲቲው የሚገኙ የትምህርት መከታተያ ህንፃዎችን ምቹ ከማድረግ አንፃር መወጣጫ  ራንፕ በመስራትና  የተለያዩ ተግባራትንም ሲከናወኑ መቆየታቸውንና በመከናወን ላይ መሆናቸውንም ገልፀዋል፡፡  በቀጣይ አዳዲስ የሚገነቡ ህንፃዎችም ሙሉ ለሙለ አካልጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ እንዲሆኑ ትኩረት ተደርጎበት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ከሌሎች ጉዳት አላባ ከሆኑ ተማሪዎች እኩል ተፎካካሪና ተጠቃሚ በመሆን ስኬታማ መሆን እንዲችሉ  ዩኒቨርሲቲው የተለያዩ የትምህርት መርጃ ቁሳቁሶችን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ገልጸው ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

ለአንድ ቀን በቆየው መድረክ ላይ ወቅታዊ የአካል ጉዳተኞች ሁኔታ ላይ ትኩረት ያደረገ ጥናታዊ ፅሁፍ ከድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽ/ቤት በመጡ ከፍተኛ ባለሞያ በወ/ሮ አዲስ አሰፋ ቀርቦ በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎበታል፡፡


Share This News

Comment