Logo
News Photo

ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ማህበራዊና ልማት ኮሚሽን የሐረርጌ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር ከምስራቅ ሀረርጌ ወረዳዎች ለተውጣጡ ወጣቶች በጨርቃጨርቅና አልባሳት ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ተጠናቀቀ፡፡

ድሬዳዋ ዪኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ማሕበራዊና ልማት ኮሚሽን የሐረርጌ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር  ከሚያዝያ እስከ ሰኔ 2016 ዓ.ም. ለሶስት ወራት ከምስራቅ ሀረርጌ አራት ዞኖች እና አስር ወረዳዎች ለተውጣጡ ለ50 ሥራ አጥ ወጣቶች  የስራ እድልን የሚፈጥር በጨርቃጨርቅና አልባሳት ክህሎት ላይ የሚያተኩር ሥልጠና ሲሰጥ የቆየ ሲሆን በዛሬው እለት ሰልጠኞቹን በደማቅ ፕሮግራም አስመርቋል፡፡ 

ፕሮግራሙን የከፈቱት የዩኒቨርሲው የምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚደንት ዶ/ር ተማም አወል ሲሆኑ ለተመራቂዎች መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ በመቀጠልም የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት ዶ/ር ኡባህ አደም  እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው  ላለፉት ሶስት ወራት ተግባራዊ ስልጠና ለወጣቶቹ ሲሰጥ የቆየ ሲሆን የገጠሩን ወጣቶች በአቅም ግንባታ እና በስራ እድል ፈጠራ ተደራሽ በማድረግ ሂደት ውስጥ ዩኒቨርሲቲው ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የጀመረው ጥረት ፍሬ በማፍራቱ እንደተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፣ ሰልጣኞች ያገኙትን ክህሎት ወደስራ በመቀየር ሂደት በትጋት እንዲንቀሳቀሱ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ማሕበራዊና ልማት ኮሚሽን  ምክትል ዳይሬክተር አቶ ግርማ ከበደ በበከኩላቸው ተቋሙ ከሚሰጣቸው ማህበራዊ አገልግሎቶች አንዱ የሴፍቲኔት ተጠቃሚ ለሆኑ ወጣቶች የስራ እድል መፍጠር መሆኑን ጠቅሰው ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በዚህ ትልቅ ተልዕኮ አጋር በመሆኑ የተሰማቸው ደስታ ገልፀዋል፡፡ በመቀጠልም ንግግር ያደረጉት ወ/ሮ ጥሩሴት ሀይሌ የስርአተ-ጾታ የወጣቶችና ማህበራዊ ዳይናሚክስ ም/ኃላፊ እንደተናገሩት ፕሮግራሙ ለወጣቶች በተለይም ለሴቶች ትልቅ ትኩረት መስጠቱ እጅግ ለየት እንደሚደርገው ገልፀው ሰልጣኞች ባገኙት ክህሎት ለውጤታማነት እንዲተጉ ምክራዊ መልዕታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በፕሮግራሙ ከተለያዩ ቀጣሪ ኢንዱስትሪዎች የተጋበዙ  ተወካዮች የተገኙ ሲሆን የተመረቁትን ሰልጣኞች በሙሉ መቀበል የሚችል የስራ ዕድል መኖሩን ገልፀው ሰልጣኞችን ለስራ ወደ ኢንዱስትሪዎቻቸው ጋብዘዋል፡፡ በምረቃው ስነስርዓት ከአራቱም  የምስራቅ ሀረርጌ ዞኖች እና አስር ወረዳዎች የተጋበዙ እንግዶች፣ አሰልጣኞች፣ የዩኒቨርሲቲው የስራ ሃላፊዎች እና ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የተሳተፉ ሲሆን፤ ስልጠናውን 37 ሴቶች እና 11 ወንዶች ባጠቃላይ 48 ወጣቶች ማጠናቀቀቃቸው ታውቋል፡፡

Share This News

Comment