Logo
News Photo

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በጦርነቱ ለተፈናቀሉና ቤት ንብረታቸው ለወደመባቸው የማህበረሰብ ክፍሎች የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ባለው ጦርነት ምክንያት ለተፈናቀሉና ቤት ንብረታቸው ለወደመባቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ያሰባሰባቸውን የተለያዩ አልባሳትና የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ለደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ አስረከበ።

በድጋፍ ርክክቡ ላይ ዩኒቨርሲቲውን በመወከል ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ወንዲፍራው ደጀኔ እንደገለፁት ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የተደቀነብንን የህልውና ስጋት ለመመከት እየተደረገ ባለው ጦርነት ችግሩ ከተፈጠረ ጀምሮ ተከታታይ ድጋፎችን እያደረገ እንዳለ ገልፀው በዛሬው እለት ለተፈናቀሉና ቤት ንብረታቸው ለወደመባቸው ወገኖቻችን ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ የተሰባሰቡትን የተለያዩ ቁሳቁሶች ለመስጠት መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡

በድጋፍ ርክክቡ ስነ-ስርአቱ ላይ 96 ኬሻ የአዋቂዎችና የህፃናት አልባሳት፤ 15 ኬሻ የአዋቂዎችና የህፃናት ጫማዎች፤ 32 ፍራሾች; 7 ካርቶን የሴቶች ንፅህና መጠበቂያና፤ 865 ሊትር ፈሳሽ ሳሙና ለደብረ-ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ተወካይ ያስረከቡ ሲሆን ዩኒቨርሲቲውና የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብም እያደረገ ያለውን ዘርፈ-ብዙ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

የደብረብረሃን ዩኒቨርሲቲን በመወከል ድጋፉን የተረከቡት አቶ ደመቀ ቀፀላ ሲሆኑ በንግግራቸውም ላይ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ የተፈናቀሉትንና ቤት ንብረታቸው የወደመባቸውን የማህበረሰብ ክፍሎች መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ርብርብ ወገናዊነታቸውንና አጋርነታቸውን ያሳዩበት  መሆኑን ገልፀው የተረከቡትን የቁሳቁስ ድጋፎች ለሚመለከታቸው የማህበረሰብ ክፍሎች እንደሚያደርሱ በዪኒቨርሲቲያቸው ስም ቃል ገብተው ለድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ከፍተኛ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

Share This News

Comment