Logo
News Photo

የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ሬድዮ ጣቢያ ለማቋቋም ጠቅላላ ጉባኤ አካሄደ፡፡

የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ቀደም ባሉት አመታት የማኅበረሰብ ሬድዮ ጣቢያ ለማቋቋም እንቅስቃሴ የጀመረ ቢሆንም በተለያዮ ምክንያቶች የጣቢያው ግንባታ ሳይከናወን ቆይቷል። ዩኒቨርሲቲው ይህንን የጣቢያ ግንባታ ለማከናወን ከአራት ወር በፊት በ9.7 ሚሊየን ብር  የሬድዮ ማሰራጫ ግንባታ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፕሬሽን ጋር ውል ስምነት ተፈራርሞ ወደ ስራ መገባቱ ይታወሳል፡፡ 

በዚህ መሰረትም ዩኒቨርሲቲው የሬድዮ ጣቢያውን ለማስጀመር የሚያስችለውን ጠቅላላ ጉባዔ በዛሬው እለት ያካሄደ ሲሆን በእለቱም የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም የተጠራውን ጠቅላላ ጉባኤ በማስመልከት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በንግግራቸውም የዚህ የሬድዮ ጣቢያ መቋቋም የማኅበረሰቡን ንቃተ-ህሊና በማሳደግ በሁሉም ዘርፍ ለውጥ እንዲመዘገብ ትልቅ እገዛ ይኖረዋል ብለዋል፡፡ 

በተጨማሪም ዶ/ር ኡባህ የጣቢያው ስራ መጀመር ዩኒቨርሲቲው ከማኅበረሰቡ ጋር ከቀድሞ በበለጠ እንዲቀራረብና በማኅበረሰቡ ዘንድ ያሉ ችግሮችንም  በጥልቀት መረዳት እንዲችል እንደሚያደርገው ገልጸው ይህ የሬድዮ ጣቢያ የተቋቋመለትን ግብ እንዲመታም ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ድጋፍ በማድረግ ከዩኒቨርሲቲው ጋር ተቀራርበው እንዲሰሩ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡ 

በዩኒቨርሲቲው የምርምርና የማኅበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሰለሞን ዘሪሁን በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ይህን የማኅበረሰብ ሬድዮ ጣቢያ ለማቋቋም የተለያዩ የማኅበረሰብ ሬድዮ ጣቢያ ያላቸውን ዩኒቨርሲቲዎችን እና የተቋማትን ልምድና ተሞክሮ እንደቀሰመ ጠቅሰው በአሁኑ ሰዓትም የሬድዮ ጣቢያውን ወደ አየር ስርጭት ለማስገባት የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል፡፡ 

ይህ የሬድዮ ጣቢያ በአሁኑ ሰዓት ስርጭት ላይ ካሉት የማኅበረሰብ ሬድዮ ጣቢያዎች እጅግ ዘመናዊና ስፊ የስርጭት አድማስ የሚኖረው መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር ሰለሞን ለድሬዳዋና ለአካባቢው ማኅበረሰብም አማራጭ የሚዲያ ተቋም በመሆን በምስራቁ የሀገራችን ክፍል የተፋጠነ ለውጥና እድገት እንዲመጣም የራሱን አስተዋፆኦ የሚያበረክት መሆኑንም ጨምረው ገልፀዋል፡፡ 

በመጨረሻም በጉባኤው ላይ የማኅበረሰብ ሬድዮ ጣቢያው መመርያ ሰነድ በመ/ር ኤርሚያስ ከጋዜጠኝነትና ኮሚንኬሽን ት/ት ክፍል ቀርቦ በተሳታፊዎች ሀሳብና አስተያየት የተሰጠበት ሲሆን በእለቱም የቦርድ አባላት ምርጫ ተካሂዷል። በዚህ መሰረትም የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም የቦርድ ሰብሳቢ ፣ ዶ/ር ሰለሞን ዘሪሁን ፣ የተከበሩ ወ/ሮ ፈጡም ሙስጠፋ ፣ አቶ ሙአዝ አሊ ፣ አቶ ፉአድ ኢብራሂም ፣ ረ/ፕ እዮብ ነጋ  እና ተማሪ ናትናኤል የቦርድ አባላት ሆነው ተመርጠዋል፡፡


Share This News

Comment