Logo
News Photo

በድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ አክሰስ የእንግሊዘኛ ቋንቋ ስኮላርሺፕ ፕሮግራም ማስጀመሪያ ስነ-ስርዓትን ተካሄደ

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ አክሰስ የእንግሊዘኛ ቋንቋ ስኮላርሺፕ ፕሮግራም (English Access Scholarship Program) ማስጀመሪያ ስነ-ስርዓት የዩኒቨርሲቲው ኃላፊዎች፣ የአሜሪካ ኤምባሲ ተወካዮች፣ የመንግስት ትምህርት ቤት ተወካዬች፣ ተማሪዎች እና የተማሪ ቤተሰቦችን ጨምሮ ከ90 በላይ ተሳታፊዎች በተገኙበት ዛሬ ህዳር 21 ቀን 2017 ዓ.ም አክብሯል።  ከህዳር 2017 እስከ መስከረም 2019 ዓ.ም. ለሁለት አመት በሚቆየው በዚህ ነፃ የትምህርት ዕድል ከስድስት የመንግስት ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ 18 ሴትና 18 ወንድ፣ በድምሩ 36 የዘጠነኛ ክፍል ተማሪዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ።

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም በመክፈቻ ንግግራቸው የፕሮግራሙ አላማዎች የተማሪዎችን የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክህሎት  ከማሳደግ በተጨማሪ፣ ለወደፊት የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸ የሚያግዝና እና በአገር አቀፍና በአለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ የማበረታታት መሆኑን አስረድተዋል።  ዶ/ር ኡባህ በተጨማሪ በፕሮግራሙ ተሳታፊ ለሆኑ ተማሪ ወላጆች ልጆቻቸው በፕሮግራሙ ስኬታማ የሆነ ጊዜ እንዲያሳልፉ ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው አሳስበው እና ፕሮግራሙ በድሬዳዋ ዩንቨርሲቲ እንዲጀመር አስተዋፅዖ ላደረጉት ለአሜሪካ ኤምባሲ እና ለዩኒቨርሲቲው የእንግሊዝኛ ቋንቋ ማሻሻያ ማእከል ምስጋና አቅርበዋል።

የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር መገርሳ ቃሲም የአሜሪካ ኤምባሲ ይህንን ፕሮግራም  በማስጀመርና  የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ላደረገው አስተዋፅዖ ምስጋና አቅርበው፣ ዩንቨርሲቲው ለፕሮግራሙ መሳካት አመቺ የመማሪያ ክፍሎችን ጨምሮ አስፈላጊውን ሁሉ ድግፍ እንደሚያረግ ገልፀዋል።  ተማሪዎችም የወደፊት ስኬታቸውን እውን ለማድረግ ይህን ዕድል በአግባቡ እንዲጠቀሙ አሳስበዋል።

በአሜሪካ ኤምባሲ የምስራቅ አፍሪካ የእንግሊዘኛ ቋንቋ ኦፊሰር (Regional English Language Officer- RELO East Africa) የሆኑት ዶ/ር ጂና ሮድስ በፕሮግራሙ መጀመር መደሰታቸውን ገልፀው ተማሪዎቹ የእንግሊዘኛ ቌንቋ ችሎታቸውን በማሻሻል የወደፊት የስራ እድላቸውን ማሳደግ እንደሚችሉ አብራርተዋል።   ተማሪዎች የአመራርና ችግር ፈቺ ክህሎትን ለማዳበር በተዘጋጁ የመስክ ተግባራት ላይ እንደሚሳተፉ ገልፀዋል።

የአክሰስ ፕሮግራም አስተባባሪ የሆኑት አቶ ነቢል መሀመድ የፕሮግራሙን ዋና ዋና መገለጫዎች፣ መርሃ ግብሮች እና ተማሪዎችን የተመረጡበትን ሂደት አስረድተው፣ ተማሪዎቹ ፕሮግራሙን በተሳካ ሁኔታ እንዲያጠናቅቁ የወላጆች ተሳትፎና እገዛ አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል። በመክፈቻ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙ የተማሪ ወላጆች በፕሮግራሙ መጀመር የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል።

በመጨረሻም የፕሮግራሙ ተሳታፊ ሆነው የተመረጡት 36 በፕሮግራሙ ተሳታፊነታቸውን የሚያረጋግጥ  ሰርተፍኬት ከዶ/ር ኡባህ እና ከዶ/ር ጂና ተረክበው ስነ-ስርዓቱ ተጠናቋል።


Share This News

Comment