Logo
News Photo

በተጋባዥ የኢንዱስትሪ ባለሙያዎች (Experts) ሲሰጥ የነበረው የአንድ ሳምንት የተግባር ትምህርት ተጠናቀቀ

የድሬደዋ ዩንቨርሲቲ ‘አንድ የማስተማሪያ ሳምንት ለኢንዱስትሪ ባለሙያ’ በሚል መሪ ቃል ሲሰጥ የነበረው የተግባር ትምህርት ተጠናቋል። ከተለያዩ ኢንዱስትሪዎች የተውጣጡ ኤክስፐርቶች በተለያዩ ት/ርት ክፍሎች ስር ለሚገኙ ተማሪዎች ተግባራዊ ትምህርት ሰጥተዋል። 

በመዝጊያ ዝግጅቱ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የዩንቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም ‘’ኢንዱስትሪዎች የተቋማችን ዋነኛ አጋሮቻችን ናቸው’’ ብለዋል። ድሬደዋ ዩንቨርሲቲ ከመንግስት የተሰጠውን ተልዕኮ ያለ ኢንዱስትሪዎች ተሳትፎ እና ትብብር ማሳካት አይችልም ያሉት ፕሬዝደንቷ በምሩቃኖቻችን ዘንድ የሚስተዋለውን የክህሎት ክፍተት ለማረም የተጀመረው የተግባር ትምህርት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል። 

ፕሬዝደንት ኡባህ በተለይ በተማሪዎች ኢንተርንሺፕ አተገባበር ዙሪያ ስለሚስተዋሉ ችግሮች አጽናኦት ሰጥተው የተናገሩ ሲሆን ‘’ኢንተርንሺፕ በበቂ ክትትል እና ድጋፍ ታግዞ ተማሪ በክፍል ውስጥ የተማረውን በተግባር እንዲሰራ፣ ልምድ እና ክህሎትም የሚያዳብርበት ሊሆን እንደሚገባ’’ ተናግረዋል። በቀጣይነት መምህራን ወደ ኢንዱስትሪዎች ሄደው በመስራት ተግባራዊ ክህሎት ያዳብሩ ዘንድ አቅደው እየሰሩ መሆኑንም የዩንቨርሲቲው ፕሬዝደንት ጠቁመዋል።

የዩንቨርሲቲው አካዳሚክ ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር መገርሳ ቃሲም በበኩላቸው የተጀመረው የተግባር ትምህርት በሰፊው እንደሚቀጥል ጠቅሰው በቀጣይነት በስራዓተ ት/ርት ክለሳ፣ በትምህር ክፍሎች እውቅና (accreditation) እና የተግባር ትምህርቶችን በተመለከተ ከኢንዱስትሪዎች ጋር በመቀናጀት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።  የድሬደዋ ዩንቨርሲቲ የአፕላይድ ሳይንስ ዩንቨርሲቲ መሆኑን ያስታወሱት የአካዳሚክ ም/ፕሬዝዳንቱ ብቁ የተማረ የሰው ሃይል ለማፍራት የአምራች እና አገልግሎት ሰጪ ኢንዱስትሪዎች ሚና የጎላ ነው ብለዋል። 

በመዝጊያ ዝግጅቱ ላይ የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ልዩ ረዳት የሆኑት ዶ/ር ግርማ ቤካ በተሰጠው የአንድ ሳምንት የተግባር ትምህርት ዙሪያ የተገኙ ስኬቶች፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እና መፍትሄ ጠቋሚ ሪፓርት አቅርበዋል። ዶ/ር ግርማ ያቀረቡትን መነሻ ጽሁፍ ተከትሎ ሰፊ ውይይት ተደርጓል። በውይይቱም ከተለያዩ ኢንዱስትሪዎች የመጡ ባለሙያዎች፣ ተማሪዎች እና የዩንቨርሲቲው አመራሮች በነበራቸው የአንድ ሳምንት ቆይታ አስተያየት ሰጥተዋል። 

የውይይቱን መጠናቀቅ ተከትሎ የድሬደዋ ዩንቨርሲቲ በተግባር ትምህርት ሂደቱ ላይ ተሳታፊ ከነበሩ ኢንዱስትሪዎች ጋር በቀጣይነት አብሮ ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል የምስጋና የምስክር ወረቀትም ለሁሉም ተሳታፊ አካላት በክብር ሰጥቷል። የፊርማ ስነ-ሥራዓቱን ተከትሎ የዩንቨርሲቲው ምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ተማም አወል የመዝጊያ ንግግር አድርገው የእለቱ መርሃ ግብር ተጠናቋል። 

Share This News

Comment