ተመራቂ ተማሪዎች በየአመቱ እንደ አንድ ኮርስ በቡድን የማህበራሰብ ጤና አገልግሎት ስራ ይሰራሉ፡፡ በዚሁ መሰረት የዚህ አመት
(2017 ዓ.ም) የ6 ትምህርት ክፍል ተመራቂ ተማሪዎች (ህክምና፤አንስቴዥያ፤ሚድዋይፍሪ፤ሳይካትሪ፤ሜዲካል ላብራቶሪ እና ነርሲንግ) ለ6 ሳምንት በሳቢያን ቀበሌ (መስቀለኛ፣ ሰባተኛ፣ ጎሮ እና ኢንዱስትሪ)፣ በ 03 ቀበሌ (ነምበርዋን) እና በጤና ጣቢያዎች ዉስጥ ሲሰሩ የነበሩትን የማህበረሰብ ጤና አገልግሎት የስራ ሪፖርት ታህሳስ 22/2017 ዓ/ም የሚመለከታቸው ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት በዩኒቨርሲቲው ቀዩ አዳራሽ አቅርበዋል፡፡
የዕለቱን መርሃ ግብር እና የኮርሱን ዓላማ በተመለከተ የኮሌጁ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ኮርፖሬት ዳይሬክተር የሆኑት ረ/ፕሮፌሰር ለገሰ አበራ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን በማብራሪያቸውም ኮርሱ ተማሪዎች የማህበረሰብ ጤና እና ጤና ነክ ችግሮችን በመለየት እንዲፈቱ ያስችላቸዋል ብለዋል።
በመቀጠልም የህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስክዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ሁሴን መሀመድ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር በማድረግ በየቀበሌዎች የተሰሩ ስራዎችን ተዘዋውረው እንደጎበኙ በመግለጽ ተማሪዎች እና መምህራኖች የነበራቸው ጠንካራ ትስስር እና የሰሩት የማህበራሰብ ጤና አገልግሎት ስራ እንዳስደሰታቸዉ ገልጻዋል።
በዚሁ ስነ-ሥራዓት ላይ የዩንቨርሲቲው አካዳሚክ ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር መገርሳ ቃሲም የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በንግግራቸውም የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የአፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ መሆኑን በመጥቀስ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የዩኒቨርሲቲው የትኩረት አቅጣጫ አንዱ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ኮሌጁን ለማጠናከር እየሰራ መሆኑን ጠቁመቃል። ዶ/ር መገርሳ በመቀጠል የጤና ሳይንስ ኮሌጅ የመውጫ ፈተናን
100% የማሳለፍ ጥሩ ተሞክሮ ያለው መሆኑን በመግለጽ በዚህ አመትም ተመሳሳይ ውጤት ስለሚጠበቅ ተማሪዎች እና መምህራን የመውጫ ፈተና ዝግጅትን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አበክረው ተናግረዋል።
በመቀጠል የአምስቱም ቡድን ተማሪዎች የማህበረሰብ አገልግሎት ተግባራቸውን ሪፖርት በተጋበዙ እንግዶችና አስተማሪዎቻቸው ፊት አቅርበው ገንቢ አስተያየቶችን ተቀብለዋል። በመቀጠልም የተሻለ አፈፃፀም ላሳዩ ተማሪዎች የምስጋና ሰርተፍኬት በዶ/ር ተማም አወል (የምርምር ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕሬዝዳንት)፣ በዶ/ር ሁሴን መሐመድ እና በረ/ፕ ለገሰ አበራ የተሰጠ ሲሆን የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክስክዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ሁሴን መሀመድ ተማሪዎች ራሳቸውን ለመውጫ ፈተና በማዘጋጀት 100% ማለፍ እንደለባቸዉ ቃል አስገብተው የእለቱ መርሃ ግብር ፍጻሜ ሆኗል።
Share This News