በተደረገው ስምምነት መሰረት የድሬደዋ ዩንቨርሲቲ መምህራን እና ተመራማሪዎች የኢፌዲሪ ትምህርት እና ስልጠና ባለስልጣን እንዲሁም የህክምና ጤና ሳይንስ ሙያ ማህበራት የእውቅና አሰጣጥ ስርዓታቸው ዲጂታላይዝ እንዲሆን የሚረዳን ተቋማዊ መተግበሪያ የሚያበለጽጉ ይሆናል።
በዚሁ የስምምነት መድረክ ላይ ንግግር ያደረጉት የድሬደዋ ዩንቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም ተቋማቸው የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የትምህርትና ስልጠና ጥራትን ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ጠቁመው የድሬደዋ ዩንቨርሲቲ በዚህ ሀገራዊ ፋይዳው የጎላ በሆነ ፕሮጀክት ላይ የራሱን አሻራ ማሳረፍ በመቻሉ መደሰታቸው ገልጸዋል። በተለይ የኢፌዲሪ የትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን የዲጂታላይዜሽን ስራ መጀመሩን አድንቀው የድሬደዋ ዩንቨርሲቲ ይህንኑ የተቋሙን ፍላጎት በመረዳት በተገባው ውል መሰረት ስራዎችን አጠናቀው ለማስረከብ በትኩረት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
የኢፌዲሪ ትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን ስታንዳርዳይዜሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ድንኳና ንጉሳ በስምምነቱ ላይ እንደተናገሩት ባለሥልጣኑ እውቅና ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት አጠናቆ ወደ ስራ መግባቱን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የሚድዋይፈሪዎች ማኅበር ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ኢብራሂም ይመር ብቁና ተወዳዳሪ ባለሙያዎችን ለማፍራት የእውቅና አሰጣጥ ሥራ በአግባቡ መስራት አስፈላጊ በመሆኑ የኢትዮጵያ የሚድዋይፈሪዎች ማኅበር ከኢፌዲሪ የትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን ጋር በመሆን የሚጠበቅበትን ድጋፍ ሁሉ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል፡፡
በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የሶፍትዊር ማበልጸግ ቡድን መሪ አቶ ጌትነት ቶሎሳ እና በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የሶፍትዊር ማበልጸግ ባለሙያ አቶ አንድነት አሰፋም እንደ ባለሙያ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ለተለያዩ ተቋማት ሶፍትዊር በማበልጸግና አገልግሎት ላይ እንዲውል በማድረግ ውጤታማ ስራ ማስመዝገቡን ገልጸው ከባለስልጣኑ ጋር በሚከናወነው የእውቅና አሰጣጥ ስርዓትን ዲጂታላይዝ የማድረግ ሥራ ከቡድናቸው ጋር በመሆን ውጤታማ ስራ ለመስራት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡
Share This News