የድሬደዋ ተወላጅ የሆኑ ዲያስፖራ ምሁራን ባላቸው እውቀትና ልምድ የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲን ለመደገፍ መዘጋጀታቸውን አስታወቁ፡፡
በተለያዩ የአለም አገራት በተለይም በምዕራብ አፍሪካ ለረጅም ዓመት በአይን ቀዶ ጥገና ህክምና ያገለገሉት ፕሮፌሰር ሞገስ ተሾመ እና በኔዘርላንድና በቤልጂየም በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በመምህርነት በማገልገል ላይ የሚገኙት ዶ/ር መሀመድአሚን ሁሴን ያካበቱትን ልምድና እውቀት ተጠቅመው የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲን በሞያቸው ለመደገፍ መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል፡፡
ምሁራኑ በተለይ ዩኒቨርሲቲው በምዕራቡ ዓለም ከሚገኙ ታላላቅ ዩኒቨርሲተዎች ጋር በማስተሳሰር በዚህም የተለያዩ ድጋፎችን እንዲያገኝና የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ መምህራን በእነዚህ ታላላቅ ዩኒቨርሲተዎች የትምህርት እድል የሚያገኙበት ሁኔታን ለማመቻቸትም የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡
በመጨረሻም የድሬደዋ ተወላጅ የሆኑት ዲያስፖራ ምሁራን በድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ በግንባታ ላይ የሚገኙትን የዘመናዊ ቤተ-መጽሐፍ እና የመካከለኛ ክሊኒክ ግንባታ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡ በዚህ ጊዜም በተለይ ክሊኒኩ በሚፈለገው መልኩ አገልግሎት መስጠት እንዲችል የህክምና ግብዓቶች እንዲሟላለት የበኩላቸውን አንቅስቃሴ እንደሚያደርጉም አስታውቀዋል፡፡
Share This News