በኢሳ ማህበረሰብ ዘንድ ለዘመናት በጥቅም ላይ የዋለው፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሻገረ ዛሬም ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን ትልቅ ሚና እየተጫወተ የሚገኘው የ ’’ሄር ኢሴ’’ ቃላዊ መተዳደሪያ ህግ እና ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት በአለም አቀፉ ትምህርት የሳይንስ እና ባህል ተቋም (UNESCO) መመዝገቡን ተከትሎ የድሬደዋ ዩንቨርሲቲ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አዘጋጅቷል።
በመድረኩ የእንኳን ደህና መጣቹ ንግግር ያደረጉት የድሬደዋ ዩንቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶ/ር ኡባህ አደም ‘’ሀገር በቀል ክንውኖች እና እውቀቶች የቀደመው ትውልድ ለገጠመው ታሪካዊ ስንክሳር መፍትሄ ከመሆኑም ባሻገር አሁን ያለው ትውልድም በአግባቡ ጠብቆ ቢያቆየው በርካታ ማህበራዊ ፋይዳዎች ይኖሩታል ሲሉ ተናግረዋል። ዶ/ር ኡባህ በማከል ‘’የሄር ኢሴ’’ ቃላዊ ህግ የኢሳ ማህበረሰብ ለብዙ መቶ አመታት ውስጣዊ አንድነቱን አጽንቶ እና ሰላሙን ጠብቆ እንዲኖር አስችሎታል’’ ብለዋል። መሰል ባህላዊ ቅርሶች ተጠብቀው እንዲቆዩ ደግሞ የተቋማት ድርሻ የጎላ ነው ያሉት ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ የድሬደዋ ዩንቨርሲቲ ‘’ሄር ኢሴን’’ ጨምሮ ሌሎች ባህሎች ትውፊታዊ ይዘታቸውን ሳይለቁ ለትውልድ እንዲሸጋገሩ የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።
በርካታ መጽሃፍትን ያሳተሙት፣ የአርታኦት ስራን የሰሩ፣ በ UNESCO በተለያዩ የሃላፊነት ቦታዎች ያገለገሉት እና አሁን ‘አፍሮስፔክቲቭ’’ የተሰኘ የሃሳብ አፍላቂዎች እና ማህበረሰብ መሪዎች ንቅናቄ መስራች እና መሪ ዶ/ር አሊ ሙሴ ጥናታዊ ጽሁፋቸውን አቅርበዋል። ዶ/ር አሊ በጥናታቸው የሄር ኢሴን ታሪካዊ ዳራ፣ ማህበራዊ ፋይዳ፣ መሰረታዊ ጸባያት እና በዩኔስክ መመዝገቡ ስለሚፈጥረው እድል ሰፊ ደሰሳ አድርገዋል።
የመድረኩ ሁለተኛ ጥናታዊ ጽሁፍ አቅራቢ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና የሲቲ ቅርስ ፋውንዴሽን መስራች እና መሪ የሆኑት የተከበሩ አያን አሊ ናቸው። የተከበሩ አያን አሊ ’’ሄር ኢሴን’’ ከዘመናዊው የፍትህ ስራዓት ጋር አነጻጸረዋል፣ ቃላዊ ህጎቹ ስላላቸው መሰረታዊ ባህሪያት አብራርተዋል እንዲሁም ህጎቹ የሴት ልጅን መብት ከመጠበቅ እና የጾታ እኩልነትን ከማረጋገጥ አንጻር ያለውን አበርክቶ በስፋት አብራርተዋል።
በዝግጅቱ ላይ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ የድሬደዋ ከተማ ነዋሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ባህላዊ ዳኞች፣ የዩንቨርሲቲ መምህራን እና ተመራማሪዎች፣ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች እና የባለ ድርሻ አካላት መሪዎች እና ተወካዮቻቸው ተገኝተው ሰፊ ውይይት ያደረጉ ሲሆን የእለቱ ጥናት አቅራቢ ዶ/ር አሊ ሙሴ የድሬደዋ ዩንቨርሲቲ ፕሬዝዳንት መድረኩ እንዲዘጋጅ ላበረከቱት አስተዋጻኦ የራሳቸውን መጽሃፍ በማስታውሻነት አበርክተውላቸዋል። ይህን ተከትሎ የእለቱ ዝግጅት በሃይማኖት አባቶች እና የጎሳ መሪዎች ምርቃት እና ምስጋና ፍጻሜውን አግኝቷል።
Share This News