በመጪው ጥር 17 ቀን
2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩንቨርሲቲ በደማቅ ስነ-ስርዓት ይጀመራል ተብሎ ለሚጠበቀው የከፍተኛ ትምህርት የስፖርት ፌስቲቫል ዝግጅትን አስመልክቶ የድሬዳዋ ዩንቨርሲቲ የተማሪዎች የስፖርት ቡድን ከሀረማያው አቻው ጋር የተለያዩ የወዳጅነት ስፕርታዊ ግጥሚያዎችን አካሂዷል፡፡
በእግር ኳሱ ሀረማያን የገጠመው የዩንቨርሲቲው የተማሪዎች የወንዶች የእግር ኳስ ቡድን እስከ እረፍት 2 ለ1 በሆነ ውጤት ሲመራ ቢቆይም ከእረፍት መልስ በተቆጠሩብት 2 ጎሎች 3 ለ 2 በሆነ ውጤት ሽንፈትን አስተናግዷል፡፡
በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩንቨርሲቲ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት(የኢትዮጵያ ዩንቨርሲቲዎች) ዓማታዊ የስፖርት ፌስቲቫል ዝግጅትን ታሳቢ በማድረግ በሀረማያና በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል ከእግር ኳስ ግጥሚያ በተጨማሪ በቴኳንዶ ፣ በቼዝ እና በገበጣ (ባህላዊ ስፖርት) ስፖርቶች የወዳጅንት ውድድሮች ተካሂደዋል፡፡
በድሬደዋ ዩንቨርሲቲ የተማሪዎች ም/ዲን የሆኑትና የፕሮግራሙ አስተባባሪ መምህር እንዳለ ሞገስ አዲስ አበባ ላይ በሚካሄደው የስፖርት ፌስቲቫል ቁጥራቸው ከ55 በላይ የሚሆኑ የስፖርት ቡድን አባላት ከቀናት በኋላ ወደ ስፍራው ያቀናሉ ብለዋል፡፡
በዚህ ፌስቲቫል ላይ ተካፋይ የሚሆነው የድሬዳዋ ዩንቨርሲቲ የስፖርት ቡድን ከውድድር ባለፈ የድሬደዋን አብሮ በፍቅርና በሰላም የመኖር አኩሪ እሴትን ያስተዋውቃል የተባለ ሲሆን ፌስቲቫሉ ከስፓርታዊ ፉክክሮች በተጓዳኝ ተማሪዎች እርስ ብእርሳቸው የሚተዋወቁበት፣ ልምድ የሚለዋወጡበት እንዲሁም ዩንቨርሲቲያቸውን የሚያስተዋውቁበት መልካም አጋጣሚን የሚፈጥር እንደሚሆን ተነግሯል፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የስፖርት ፌስቲቫል በፀጥታ እና ተያያዥ ምክንያቶች ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ተቋርጦ የነበረ ሲሆን ዘለግ ካለ ዓመታት በኃላ ዘንድሮ በተለያዩ የስፓርት አይነቶችን እና በርካታ የመንግስት ዩንቨርሲቲዎችን ባሳተፈ መልኩ እንደሚካሄድ ታውቋል።
Share This News