የድሬደዋ ዩንቨርሲቲ ከ ድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው እና በ ‘ሔር ኢሴ’’ ያልተጻፈ ህግ እና ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት ላይ ትኩረቱን ያደረገ የውይይት መድረክ ዛሬ የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር፣ የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት ሙስጠፌ መሀመድ፣ የቱሪዝም ሚንስትር ሰላማዊት ካሳ፣ የሶማሌ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኢብራሂም ኡስማን፣ የጅቡቲ ወጣቶችና ባህል ሚንስተር ዶ/ር ሂቦር ሞሚን አሶዌ፣ የሶማሊያ ሚንስትሮች፣ የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች እንደዚሁም በርካታ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች አባገዳዎች ኡጋዞች የሀገር ሽማግሌዎች በተገኙበት ተካሂዷል።
በዝግጅቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ‘’ሔር ኢሴ የኢሳ ማህበረሰብ ለዘመናት እሴቱ አድርጎ ያቆየው እና አስከዛሬ ድረስ ውስጣዊ አንድነቱን ለማጽናት የሚገለገልበት አኩሪ ባህሉ ነው’’ ብለዋል።
በመድረኩ የተገኙት እና ንግግር ያደረጉት የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት ሙስጠፌ መሀመድ ሔር ኢሴ በአለም አቀፍ መድረክ እውቅና ማግኘቱ ለመላው የኢሳ ማህበረሰብ፣ ለሱማሌ ህዝብ እና ለመላው የሀገራችን ህዝቦች ትልቅ ኩራት መሆኑን በመናገር ባህላዊ ቅርሱ እንዲመዘበብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላደረጉ የክልል፣ የፌደራል እና አለም አቀፍ ተቋማት ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በዝግጅቱ ላይ የሔር ኢሴን ታሪካዊ ዳራ፣ የጻታ ተሳትፎ፣ የባህሉ መገለጫ ባህሪያት እና ከዘመናዊ የህግ ስርዓት ጋር ስላለው አንድነት እና ልዩነት የሚዳስ ሱ ሶስት ጥናታዊ ጽሁፎች የቀረቡ ሲሆን ጥናታዊ ጽሁፎቹን በአወያይነት የተከበሩ አምባሳደር መሀሙድ ድሪር መርተውታል።
Share This News