Logo
News Photo

የድሬደዋ ተወላጅ የሆኑ ዲያስፖራዎች የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ በ2030 በአፍሪካ ተመራጭና ተወዳደሪ ዩኒቨርሲቲ የመሆን የያዘውን ርዕይ እንዲያሳካ የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ፡፡

ዛሬ የድሬደዋ ተወላጅ የሆኑ ዲያስፖራዎችን ለመቀበል በተዘጋጀው ፕሮግራም ላይ በመገኘት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ከዚህ ቀደም ለእድገቱ ሳንካ ሆነው የቆዩበትን ችግሮች ደረጃ በደረጃ በመቅረፍ በአሁኑ ሰዓት በተፋጠነ የለውጥና የአድገት ጎዳና ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው የአፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ በመሆን  በቴክኖሎጂውና በኢንደስትሪው ዘርፍ ብቁና የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት ድሬደዋ የምስራቁ ክፍል ዋነኛ የኢንደስትሪ ኮሪደር የመሆን ርዕይን ለማሳካት የምታደርገውን እንቅስቃሴ ከዳር ለማድረስ የበኩሉን አስተዋፆኦ እየተወጣ እንደሆነ ዶ/ር ኡባህ አብራርተዋል፡፡ 

ዶ/ር ኡባህ አክለው ዩኒቨርሲቲው በ2030 ከአፍሪካ ተመራጭና ተወዳደሪ ዩኒቨርሲቲ የመሆን ርዕይን ሰንቆ ከመቼው ጊዜ በላይ በሁሉም መስክ መጠነሰፊ እንቅስቃሴ  ላይ መሆኑንና ኑሯቸውን በውጪ ያደረጉና የድሬደዋ ተወላጅ የሆኑ ዲያስፖራዎች ዩኒቨርሲቲውን በተለያዩ አገራት ከሚገኙ ታላላቅ ዩኒቨርሲተዎች ጋር በማስተሳሰርና በቻሉት አቅም በመደገፍ የበኩላቸውን ይወጡ ዘንድ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የድሬደዋ ዲያስፖራ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አቤለ አሸብር በበኩላቸው እንደገለጹት ብቸኛው ሃብታችን የሆነውን ዩኒቨርሲቲያችንን መደገፍ የድሬደዋን ማህበረሰብ መደገፍ ነው ያሉ ሲሆን የዲያስፖራው አባልትም ለዩኒቨርሲቲው አንባሳደር በመሆን አለም አቀፍ ተቀባይነት እንዲኖረው የበኩላቸውን እንዲወጡ  ጠይቀዋል፡፡ 

በፕሮግራሙ ላይ ተሳታፊ የሆኑ የድሬደዋ ተወላጅ ዲያስፖራዎች በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት በሚችሉት ሁሉ የዩኒቨርሲቲው ርዕይ እውን እንዲያደርግ ድጋፍ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል፡፡

በመጨረሻም የዲያስፖራ አባላቱ በድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ስር የሚገኘውንና ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ ያለውን   የድሬደዋ ሪፈራል ሆስፒታል ጎብኝተዋል፡፡

Share This News

Comment