Logo
News Photo

ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው 10ኛው ሀገር አቀፍ የምርምር ኮንፍረንስ ተጠናቋል

19 ምምሮች እና 4 ተጋባዥ እንግዶችን ያሳተፈው 10ኛው ሀገራዊ የምርምር ኮንፍረንስ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል። ኮንፍረንሱ በተለይ በመጀመሪያው ቀን ውሎው 4 ስመ ጥር ተመራማዊዎች በተመረጡ ርዕሶች ዙሪያ ቁልፍ ንግግሮችን ያደረጉበት ሲሆን ሀገራዊ እና ነባራዊ ችግሮችን ለመፍታት መፍትሄ የሚሆኑ ሀሳቦችም ተነስተውበታል። 

ተመራማሪዎቹ በተለይ ከኤሌክትሮኒክ መኪና፣ ችግር ፈቺ ምርምሮችን እና ወቅታዊውን የመዋለ ንዋይ ገበያ (stock market) በተመለከተ ጥናትን መሰረት ያደረገ ቁልፍ ንግግር አድርገዋል። ቁልፍ ንግግሮቹን ተከተሎ ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲሆን ከተሳታፊዎች የተነሱ ጥያቄዎችን ተመራማሪዎቹ ምላሽ ሰጥተውበታል። 

ኮንፍረንሱ በየካቲት 13 ቀን ከሰዓት እና የካቲት 14 ቀን ጠዋት ውሎው የተለያዩ ተመራማሪዎች ይዘው የቀረቡትን 19 የምርምር ወጤቶች ከከተማ አስተዳደሩ ለተጋበዙ ባለድርሻ አካላት እና ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በማቅረብ የቀጠለ ሲሆን ለበርካታ ማህበራዊ፣ አኮኖሚያዊ ጉዳዮች መፍትሄ ጠቋሚ ምክረ-ሃሳቦች በሰፊው ተመላክተውበታል። 

በትምህርት ሚኒስቴር የምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር ዶ/ር ሰራዊት ሀንዲሶ ‘’በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ምርምሮች እንደሚሰሩ ጠቁመው በአፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲዎች የሚሰሩ ምርምሮች ግን በምርምር ይዘት እና ውጤት (end result) ይለያሉ’ በማለት ተናግረዋል። ዶ/ር ሰራዊት በማከለም የአፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲዎች ተጨባጭ ችግሮችን በተለይ ምርት እና ምርታማነትን ከማሳደግ አንጻር እንዲሁም በኢንዱስትሪዎች አካባቢ የሚታዩ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን በመቅረፍ ሂደት ውስጥ ሚና ሊኖራቸው እንደሚገባ’ አስገንዝበዋል። 

በኮንፍረንሱ መዝጊያ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ የምርምር፣ ማህበረሰብ አገልግሎት እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ተማም አወል እንደተናገሩት ‘የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ችግር ፈቺ እና ጭብጥ ተኮር ምርምሮችን በማድረግ ቀዳሚ ዩኒቨርሲቲ ለመሆን እንደሚሰራ’ አመልክተው በተለይ ከተቋማት ጋር በትብብር የሚሰሩ ምርምሮችን ዩኒቨርሲቲው ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ገልጸዋል። ዶ/ር ተማም ከተለያዩ ቦታዎች የዩኒቨርሲቲውን ጥሪ አክብረው ለመጡ ተመራማሪዎች ምስጋና አቅርበዋል። 

የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ለሁለት ቀናት በተደረገው ሀገራዊ የምርምር ኮንፍረንስ ላይ ለተሳተፉ ተጋባዥ እንግዶች እና ተመራማሪዎች የምስጋና የምስክት ወረቀት ሰጥቷል። 


Share This News

Comment