የዛሬ ዓመት የካቲት 17 2016 ዓ/ም ተመርቆ ስራ የጀመረው የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ማተማሪያ ሪፈራል ሆስፒታል አንደኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች እና የሆስፒታሉ ሰራተኞች እና መምህራን በተገኙበት በድምቀት ተከብሯል። የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ የሆስፒታል ግንባታ ስራውን ከድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ተረክቦ በማጠናቀቅ እንዲሁም ሆስፒታሉ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስፈልጉትን ቁሳቁሶች በማሟላት ልክ የዛሬ ዓመት ስራ ማስጀመር ችሏል።
ይህንኑ በማስመልከት በተዘጋጀው የምስረታ በዓል ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ም/ፕሬዝዳንት እና የፕሬዝዳንት ተወካይ የሆኑት ዶ/ር መገርሳ ቃሲም ‘’ማስተማሪያ ሪፈራል ሆስፒታሉን ግንባታ አጠናቆ ስራ ለማስጀመር የዩኒቨርሲቲው ማናጅመንት ከፍተኛ ድርሻ ነበረው ያሉ ሲሆን በቀጣይም ሆስፒታሉን በሰው ሃይል እና ቁሳቁስ በማደራጀት ለአካባቢው ማህበረሰብ ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
የሆስፒታሉን ታሪካዊ ዳራ እና አሁናዊ መረጃ በመስጠት ንግግር ያደረጉት የሆስፒታሉ ቺፍ ኤክስኩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ሁሴን መሀመድ በበኩላቸው ‘’ ሆስፒታሉን ስራ ለማስጀመር እርሳቸውን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት እና የህክምና ጤና ኮሌጅ መምህራን በክፍተኛ ቁርጠኝነት መስራት መቻላቸውን አውስተው በተለይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም ሆስፒታሉ ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጥ በማድረግ ሂደት ውስጥ ላሳዩት በሳል አመራር እና ቁርጠኝነት በራሳቸው እና በመላው የሆስፒታሉ ሰራተኞች ስም አመስግነዋል።
ሆስፒታሉ ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ መምህራን ተቀናጅቶ መበስራት፣ ከሙያዊ ስራ ውጪ የአስተዳደር ስራዎችን ጭምር ደርቦ በመስራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል ያሉት ደግሞ የምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ተማም አወል ናቸው። ዶ/ር ተማም ‘ዛሬ ከትላን ይሻላል ነገን ደግሞ ከዛሬ የተሻለ ለማድረግ ተባብረን ልንሰራ ይገባል’’ ብለዋል።
የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ማስተማሪያ ሪፈራል ሆስፒታል በውስን አቅም፣ የግብዓት አቅርቦት ውስንነት እና የሰው ሃይል እጥረት ሳይገድበው በአንድ አመት ውስጥ ለ6000 ሰዎች የህክምና አገልግሎት መስጠት የቻለ ሲሆን በቀጣይም 229 የህክምና ባለሙያዎችን እና አስተዳደር ሰራተኞችን በመቅጠር አገልጎሎቱን በስፋት እና በጥራት ለመስጠት መዘጋጀቱን ለመረዳት ተችሏል። ሆስፒታሉ ተጠናቆ ስራ እንዲጀምር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አመራር እና መምህራን የእውቅና ሰርተፊኬት ተሰጥቷል።
Share This News