Logo
News Photo

በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ "4ኛው የኢንደስትሪ አብዮት" በሚል ሀገራዊ ኮንፈረንስ ተካሄደ፡፡

በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስና ኮምፒውቱሽናል ኮሌጅ አዘጋጅንት የተካሄደው ሀገራዊ ኮንፈረንስ በዩኒቨርሲቲው ደረጃ ለ7ኛ ጊዜ ሲሆን በኮሌጅ ደረጃ ደግሞ ለ2ኛ ጊዜ የተካሄደ ነው፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ በተዘጋጀው ኮንፈረንስ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም እንደገለጹት ዓለማችን ዛሬ ለደረሰችበት የእድገት እና የስለጣኔ ማማ ትልቁን ድርሻ ባበረከተው ሳይንስ ላይ ጥናትና ምርምር ማድረግ ለሃገርም ሆነ ለአካባቢያችን እድገትና ለውጥ ያለው ፋይዳ የጎላ መሆኑን ገልፀው ይህ ሀገራዊ ኮንፈረንስ በዩኒቨርሲቲያችን መዘጋጀቱ ወጣት ተመራማሪ መምህራኖቻችን ልምድና እውቅና ካላቸው ተመራማሪዎች የሚቀስሙበት እና ትስስር የሚፈጥሩበት መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሰለሞን ዘሪሁን በበኩላቸው በሳይንስ ትምህርት ላይ ጥልቅ የሆነ ግንዛቤና መረዳት ካለን አዳዲስና የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ሀገራችንና ወደ አካባቢያችን በማምጣት ጠቃሚ ስራ መስራት ስለሚያስችለን ትኩረት አድርገው የሚሰሩ የጥናትና የምርምር ስራዎች የሚያበረክቱት ድርሻ እጅግ የጎላ መሆኑን ጠቅሰው በዚሁ ዘርፍ የሚደረጉ የጥናትና ምርምር ስራዎች በስፋት እንዲካሄዱ በማድረግ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ዩኒቨርሲቲው የበኩሉን ጥረት ያደርጋል ብለዋል፡፡

ለሁለት ቀን በቆየው ሀገራዊ ኮንፈረንስ ላይ ስምንት  አዳዲስ እና የተሻሻሉ የቴክኖሎጂ የጥናትና የምርምር ስራዎች ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲ በመጡ ተመራማሪዎች የቀረቡ ሲሆን በኮንፈረንሱ ላይ ቁጥራቸው 130 በላይ ተሳታፊዎች የታደሙ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ 


Share This News

Comment