የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እና የድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጠና በትብብር ያዘጋጁት 3ኛው ቴክኖሎጂ ነክ ምርምሮች ኮንፍረንስ በርከት ያሉ ተጋባዥ እንግዶች፣ የዩኒቨርሲቲው እና የነጻ ንግድ ቀጠናው ሰራተኞች እና አመራሮች እንዲሁም ተመራማሪዎች በተገኙበት ተጀምሯል።
ሀገር አቀፍ የምርምር ኮንፍረንሱ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የዩንቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ተወካይ ዶ/ር መገርሳ ቃሲም እንደተናገሩት ‘’የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ አፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ እንደመሆኑ ከአምራች እና አገልግሎት ሰጪ እንዱስትሪዎች ጋር ተቀራርቦ የመስራት ፈላጎት እንዳለው ገልጸው በተለይ ዩኒቨርሲቲው ከቅርብ ግዜ ወዲህ የኢንዱስትሪ ሳምንት በሚል መርሃ ግብር በርካታ የኢንዱስትሪ ባለሙያዎችን ጋብዞ በተግባር የተደገፈ ትምህርት ተማሪዎች እንዲማሩ ማድረግ መጀመሩን’’ ገልጸዋል።
በዚሁ መድረክ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ኤክስኩቲቭ ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ገደፋየ በበኩላቸው ‘’የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በርካታ ኢንዱስትሪ ተኮር እንዲሁም ለማህበረሰቡ እና ሀገር ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያላቸውን ስራዎች ማበርከት፣ የአምራች እንዱስትሪውን ዘርፍ የሚያግዙ መፍትሄ አምጪ ምርምሮችን በስፋት እየሰራ መሆኑን’’ ጠቁመዋል።
Share This News