Logo
News Photo

በድሬዳዋ አስተዳደር የመንገድ ላይ የትራፊክ አደጋን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚና ሊጠናከር እንደሚገባ ተጠቆመ።

የድሬደዋ ዩኒቨርስቲ ከድሬደዋ አስተዳደር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ባለስልጣን የመንገድ ትራፊክ ደህንነት እና መድህን ፈንድ ዳይሬክቶሬት ጋር በመቀናጀት  በመንገድ ደህንነት እና በትራፊክ አደጋ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር የምክክር መድረክ ተካሄደ።

በመንገድ ትራፊክ አደጋ በየአመቱ አለማችን 1.3ሚሊየን ሰዎችን ስታጣ በሀገራችን በሺዎች ሚቆጠሩት በትራፊክ አደጋ ሳቢያ እንደወጡ ይቀራሉ። ይህንኑ መነሻ በማድረግም እንደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም በድሬ ዳዋ የተለያዩ ማህበራዊ ኃላፊነቶቹን በመወጣት ላይ የሚገኘው የድሬ ዳዋ   ዩኒቨርስቲ ከድሬ ዳዋ አስተዳደር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ባለስልጣን የመንገድ ትራፊክ ደህንነት እና መድህን ፈንድ ዳይሬክቶሬት ጋር በመቀናጀት ለመንገድ ትራፊክ አደጋ መንስኤ የሆኑ   ችግሮች እና መፍትሄዎቹ ላይ የሚመክር መድረክ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ አካሂዷል።

በድሬ ዳዋ ዩኒቨርስቲ  የማህበረሰብ ተሳትፎ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወንድይፍራው ደጀኔ (ዶ/ር) ዩኒቨርሲቲው ከዚህ በፊትም የመንገድ ላይ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ያግዛሉ ያላቸውን ጥናቶች በማካሄድ እና ለመረጃ አሰባሰብ አጋዥ  ሶፍቱዌሮችን በማበልፀግ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው የለቱ መድረክም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጥልቀት በመምከር ለመፍትሄው በጋራ ለመስራት በሚያስችሉ መንገዶች ላይ ለመምከር የተዘጋጀ ስለመሆኑ አንስዋል። በቀጣይም ይህ ቅርርብ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።  

በባለስልጣኑ የመንገድ ትራፊክ ደህንነት እና መድህን ፈንድ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ተወካይ እና በክፍሉ የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ህግ ትግበራና ኢንስፔክሽን ቡድን መሪ አቶ ቢኒያም ጎንደር በበኩላቸው ዘርፉ በቅንጅት ስራ ውጤት ሚመጣበት እንደመሆኑ ዩኒቨርስቲው ያለውን ቅርርብ ለማጠናከር እና በሚፈለገው ሁሉ በመደገፍ ከጎናቸውን በመሆኑ እናመሰግናለን ብለዋል። በዘርፉ ውጤት ለማምጣት ጥናት ላይ የተመሰረቱ እና ያሉ ችግሮች ተፈትሸው ሚሰሩበት ስርአት ወሳኝ መሆኑን ያነሱት አቶ ቢኒያም የመንገድ ላይ የትራፊክ አደጋን ለመከላከል  ከድሬ ዳዋ ዩኒቨርስቲ ጋር የተጀመሩ  ስራዎች በቀጣይም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል። 

በመድረኩ በአቶ ቢኒያም ጎንደር እና በዩኒቨርስቲው የህግ ት/ቤት መምህር  አቶ ስምኦን ተስፋዬ በትራፊክ አደጋ አሁናዊ መረጃዎች እና ለመከላከል በሚያግዙ መንገዶች ላይ ጥናታዊ ፅሁፍ ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል።

Share This News

Comment