Logo
News Photo

ሀገራዊው የመውጫ ፈተና በስኬት ተጠናቋል

ሀገራዊው የመውጫ ፈተና ላለፉት 10 ቀናት በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ሲሰጥ የቆየ ሲሆን ፈተናው ያለምንም እንከን እና የፈተና ደንብ እና ስነ-ምግባርን በጠበቀ መልኩ ተሰጥቶ ተጠናቋል፡፡

ፈተናው በድምሩ ለ 3544 ተማሪዎች የተሰጠ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 2816 ለመጀመሪያ ጊዜ ፈተናውን የወሰዱ እንዲሁም 728 ተማሪዎች የመውጫ ፈተናውን ለሁለተኛ ጊዜ የወሰዱ ናቸው፡፡ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የፈተና ማዕከል ከተፈተኑ ተማሪዎች ውስጥ 2110 ተማሪዎች በተለያዩ መርሃ ግብሮች በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሲሆኑ የተቀሩት ተፈታኞች ከተለያዩ የመንግስት እና የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመጡ ናቸው፡፡

ዩኒቨርሲቲው ፈተናው ያለምንም ችግር ተሰጥቶ ይጠናቀቅ ዘንድ በርካታ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ፈተናው በበይነ መረብ ከመሰጠቱ አንጻር ለዚሁ አውድ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን የማሟላት፣ የኮምፒተር ላብራቶሪዎችን ማዘጋጀት፣ ተፈታኞችን ለፈተና የማዘጋጀት፣ ተከታታይ መረጃዎችን የመስጠት እንዲሁም በፈተና ስፍራዎች አካባቢ በቂ ቁጥጥር እና ጥበቃ የማድረግ ሰፊ ስራ ሰርቷል፡፡ 

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ማኔጅመንት ሀገራዊው የመውጫ ፈተና በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ የድርሻቸውን ለተወጡ አካላት ሁሉ ላቅ ያለ ምስጋና እያቀረበ ተፈታኝ ተማሪዎች መልካም ውጤት ይገጥማቸው ዘንድ ልባዊ መኞቱን ይገልጻል፡፡

Share This News

Comment