የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ አለም አቀፍ እውቅና ያላቸውን ሳይንቲስቶች እና ተመራማሪዎችን በመጋበዝ ጥናትን መሰረት ያደረጉ ንግግሮች እንዲሁም ምሁራዊ ውይይቶች እንዲደረጉ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ሲሆን በዚሁ መሰረት በአርኪዮሎጂ የጥናት ተልዕኮዎች
(expeditions) ተሳትፎ የነበራት ተመራማሪ ሬይሞንዶ ቦኒፌይ በዩኒቨርሲቲው ተገኝተው ገለፃ አድርገዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የፕሬዝዳንት ተወካይ የሆኑት ዶ/ር መገርሳ ቃሲም እንደተናገሩት ኢትዮጲያ የሰው ዘር መገኛ እንዲሁም የበርካታ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ መስህቦች ባለቤት በመሆኗ የአርኪዮሎጂ ጥናቶች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ገልፀዋል። ዶ/ር መገርሳ ቃሲም በማከልም የሉሲ ወይም ድንቅነሽ ቅሪተ አካል (fossil) ኢትዮጲያን ለዓለም ከማስተዋወቅ አንፃር የነበረው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልፀው ከዛሬ 55 ዓመት በፊት በተደረገው ታሪካዊ የአርኪዮሎጂ ጥናቶች ላይ ተሳትፎ ያደረገችው ተመራማሪ በዩኒቨርሲቲያችን በመገኘት ገለፃ በማድረጋቸው ምስጋና አቅርበዋል።
የእፅዋት፣ ስነ ህይወት እና ስነምህዳር ተመራማሪ የሆኑት እና ሉሲን ወይም ድንቅነሽን በቁፋሮ ባገኘው እና በዶናልድ ጆንሰን በተመራው የምርምር ቡድን ውስጥ ድርሻ የነበራት ሬድሚንድ ቦኒፌይ የሉሲን ቅሪተ አካል ለመፈለግ በተደረገው ጥናት ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በተለይ ተመራማሪዎች ለምን የአፋር ሃዳር ዝቅተኛ ቦታን እንደመረጡ፣ የጥናቱን አጠቃላይ ሂደት እና ሉሲ በተገችበት ሁኔታ ዙሪያ ሰፊ ገለፃ አድረገዋል።
ሬድሚንድ ቦኒፌይ ከዚህ ጥናት በተጨማሪ በርካታ ምርምሮችን በማድረግ አለም አቀፍ እውቅናን ያተረፈች ሲሆን በተለያዩ ሚዲያዎች በመቅረብ ሳይንሳዊ ትንታኔዎችን በመስጠት ትታወቃለች። በተለይ በአፋር አርኪዮሎጂካዊ ጥናቶች ላይ የነበራትን ተሳትፎ እና የምርምሩን ሂደት በጥልቀት የሚዳስሰውን መፅሃፏን በአማርኛ ቋንቋ በማስተርጎም ለንባብ እንዲበቃ አድርጋለች።
የውይይት መርሃ ግብሩን የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና ፕሮጀክት ጉዳዮች አለም አቀፋዊነት እና አጋርነት ዳይሬክቶሬት እና በፈረንሳይ-ኢትዮጲያ የአፍሪካ ቀንድ ሰባዓዊ መስተጋብሮች ጽ/ቤት በትብብር አዘጋጅተውታል።
Share This News