የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ስቴም ማእከል (STEM Center) በየዓመቱ የሚያዘጋጀውና በአስተዳደሩ ሥር በሚገኙ የ1ኛና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች መካከል በዙር ሲደረግ የነበረው የጥየቄና መልስ ውድድር ተጠናቀቀ፡፡
በአራተኛዉና የመጨረሻ ዙር በሆነው የአሸናፊዎች አሸናፊ የጥያቄና መልስ ውድድር ላይ በመገኘት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ ተሳትፎ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ወንዲፍራው ደጀኔ እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲው በሳይንስና ሒሳብ የትምህርት አይነቶች ከፍተኛ ዝንባሌ ያላቸውንና በምርምር ስራ አዲስ ግኝት መፍጠር የሚችሉ ተማሪዎችን ለማፍራት የበኩሉን እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው የዘንድሮው ውድድር ከታህሳስ 16/2017 ዓ.ም ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ዙሮች በ8ኛ፣ 11ኛ፣ 12ኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል በሳይንስና ሒሳብ የትምህርት አይነቶች ሲያካሂድ ቆይቶ ዛሬ አራተኛዉና የመጨረሻዉ ዙር የአሸናፊዎች አሸናፊ ዉድድር ላይ ደርሷል ብለዋል።
ዶ/ር ወንዲፍራው አያይዘውም የዚህ ውድድር ዋና አላማ የ1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ተማሪዎችን የሳይንስና የሒሳብ ትምህርቶች እዉቀትና ክህሎት ማሳደግ፤ የመማር ፍላጎትን መጨመር፤ ለክልላዊና ሀገር-አቀፍ ፈተናዎች ማዘጋጀት፤ እንዲሁም በተማሪዎችና በትምህርት ቤቶች መካከል አዎንታዊ የዉድድር ስሜት መፍጠርና ግንኙነታቸዉን ማጠናከር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በውድድሩ ከ20 በላይ ትምህርት ቤቶችና ከ366 በላይ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የተሳተፉ ሲሆን በሶስቱም የውድድር ዘርፍ ከ1ኛ-3ኛ ደረጃ ለወጡ ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማትና የእውቅና ሰርተፍኬት ተበርክቶላቸዋል፡፡
Share This News