Logo
News Photo

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም የምስጋና መልዕክት

የ12 ክፍል የመልቀቂያ ፈተና በሀገር አቀፍ ደረጃ እና በተለያዩ የመፈተኛ ጣቢያዎች ከሰኔ 23 2017 ዓ/ም ጀምሮ ሲሰጥ ቆይቷል። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፈተናዎቹን የማስፈተን እና የማስተባበር ተልዕኮ በመውሰድ ሀገራዊ ግዴታቸውን በአግባቡ በመወጣት ላይ ይገኛሉ። በዚሁ መሰረት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ 3,141 ተፈታኞችን ተቀብሎ መመሪያን መሰረት ባደረገ መልኩ እና በጥብቅ ዲሲፕሊን ላለፉት ሁለት ሳምንታት ሀገራዊ የመልቀቂያ ፈተናውን መስጠት ችሏል።

ፈተናው ያለምንም እክል እንዲካሄድ ዩኒቨርሲቲያችን የቅድመ ፈተና፣ የፈተና ወቅት እና የድህረ ፈተና ተግባራትን በመለየት ሰፊ ስራ ሲሰራ ቆይቷል። በተለይ የበይነ መረብ (online) ተፈታኞች የኢንተርኔት መቆራረጥ፣ የኮምፒተር እክል እና መሰል ችግሮች እንዳይከሰቱ በማሰብ  ከወራት በፊት የዝግጅት ስራዎችን ሰርቷል። ተማሪዎች ፈተናው ከመሰጠቱ ቀደም ብሎ ልምምድ እንዲያደርጉ እንዲሁም የሞዴል ፈተና እንዲፈተኑ በማድረግ በፈተና ወቅት የሚፈጠርን መደነጋገር ማስቀረት ችሏል። በመሆኑም በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የተሰጠው የበይነ መረብ ፈተና ያለምንም ችግር መጠናቀቅ ችሏል። 

የወረቀት ፈተና አሰጣጥንም በተመለከተ ከአስተባባሪዎች እና ፈታኞች ጋር ውይይት በማድረግ፣ ፈተናዎችን በጥብቅ ዲሲፕሊን እንዲጠበቁ የማድረግ እና ተተግዳሮቶችን አስቀድሞ በመለየት ዝግጅት ተደርጓል። 

የተማሪዎች መኝታ፣ የመመገቢያ፣ የላይብራሪ እንዲሁም የህክምና ክሊኒክ ለተፈታኞች ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል የቅድመ ፈተና ዝግጅትም በሰፊው ተደርጓል። ከመደበኛ አገልግሎቶች በተጨማሪ ለተማሪዎች አገልግሎት የሚሰጡ ካፍቴሪያ እና የመዝናኛ ስፍራዎችም ተመቻችተዋል። 

የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራር ባለፉት ሁለት ሳምንታት ከመፈተኛ ስፍራዎች ሳይጠፉ ጥቃቅን ችግሮችን ሳይቀር አፋጣኝ መፍትሄ በመስጠት ፈተናው ህግ እና ስርዓቱን ጠብቆ እንዲካሄድ አስችለዋል። በተለይ ኩረጃን ከማስቀረት አንፃር አስቀድሞ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን በማዘጋጀት፣ በግቢ መግቢያ እና መውጫ አካባቢ እንዲሁም መፈተኛ  አካባቢ ከፍተኛ ቁጥጥር እና ፍተሻ በማድረግ ፈተናው ትምህርት ሚኒስቴር ባስቀመጠው ደንብ እና መመሪያ እንዲተገበር ተደርጓል።

የፈተና ስፍራዎች ፀጥታቸው ተጠብቆ እና ሰላማዊ እንዲሆኑ በተለይ የፌዴራል ፓሊስ አባላት ከፍተኛ ሚና በመጫወታቸው በዚሁ አጋጣሚ ላቅ ያለ ምስጋናዬን እያቀረብኩ ዩኒቨርሲቲያችን የተሰጠውን ሀገራዊ ተልዕኮ በአግባቡ እንዲወጣ ቀን ከሌት ለለፉ የዩኒቨርሲቲያችን አመራሮች፣ የፈተና አስፈፃሚዎች፣ ኮሚቴዎች፣ አስተባባሪ እና ፈታኞች፣ የምድረ ግቢ ፀጥታ ሰራተኞች እንዲሁም ለተፈታኝ ተማሪዎቻችን በሙሉ ልባዊ ምስጋናዮን አቀርባለሁ። 

ውድ የ12ኛ ክፍል ሀገራዊ የመልቀቂያ ፈተና ተፈታኝ ተማሪዎች

ሀገራዊ የመልቀቂያ ፈተናው በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ የእናንተም ሚና ጉልህ ነበር። ዩኒቨርሲቲው ለሚከተለው ጥብቅ ዲሲፕሊን ተገዢ በመሆን እንዲሁም መመሪያን በተገቢው ሁኔታ ተግባራዊ በማድረግ ላሳያችሁት ትብብር በራሴ እና በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ስም ምስጋናዬን እያቀረብኩ የፈተና ውጤታችሁ ያማረ እንዲሆን መልካም ምኞቴን እገልፃለሁ። 

አመሰግናለሁ!!

Share This News

Comment