Logo
News Photo

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የስራ አመራር ቦርድ የ2017 ዓ/ም እቅድ አፈፃፀምን እና የ2018 ዓ/ም እቅድን ገምግሞ አፀደቀ። ቦርዱ በተለያዩ ተቋማዊ ጉዳዮችም ላይ ተወያይቶ አቅጣጫ አስቀምጧል።

ዛሬ ሐምሌ 10 ቀን 2017 ዓ/ም የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የስራ አመራር ቦርድ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ወሳኔ አስተላልፏል። ቦርዱ በዋናነት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በ2017 ዓ/ም በመማር ማስተማር፣ ምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት እንዲሁም አስተዳደር ነክ ተግባራቶች ላይ ያከናወናቸውን የእቅድ አፈፃፀም በመገምገም ያፀደቀ ሲሆን የዩኒቨርሲቲውን የ2018 ዓ/ም እቅድንም በመገምገም አፅድቋል። ቦርዱ በ2018 የበጀት ዓመት ትኩረት ተሰጥቷቸው ሊሰሩ የሚገባቸውን አንኳር ተቋማዊ ጉዳዮችንም አመላክቷል።

የዩኒቨርሲቲው የስራ አመራር ቦርድ የተከታታይ እና ርቀት ትምህርት መመሪያን ለማሻሻል የተዘጋጀ ሰነድ ቀርቦለት የተወያየ ሲሆን ቀድሞ የነበረው መመሪያ ለረዥም ጊዜ ጥቅም ላይ በመዋሉ እና ወቅቱን ያገናዘበ የስራ መመሪያ የሚያስፈልግ መሆኑን በመጠቆም የቀረበውን የተከታታይ እና ርቀት ትምህርት መመሪያ እና ስራ ማስፈፀሚያ ሰነድ በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።

በሌላ በኩል የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የአፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ ለመሆን በሚያስችለው የሽግግር ስራዎች ዙሪያ አራት ጥናታዊ ሰነዶች ተዘጋጅተው ለቦርዱ ቀርበዋል። ቦርዱም ሁሉንም ሰነዶች በመገምገ እና መሻሻል የሚገባቸው ሀሳቦችን በመስጠት አፅድቋል። የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በቀጣይ ጥናታዊ ሰነዶቹን መሰረት በማድረግ ወደ ትግበራ እንዲገባም አቅጣጫ ተቀምቷል።

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የስራ አመራር ቦርድ በሌሎች ተቋማዊ ጉዳዮች ላይም በመያየት አቅጣጫ በማስቀመጥ ስብሰባውን አጠናቋል።

Share This News

Comment