የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ተቋማትን የሚያዘምኑ ቴክኖሎጂዎችን በማበልፀግ እና ድጋፍ በማድረግ በርካታ ስራ እየሰራ ሲሆን የአስተዳደሩን ትምህርት ቢሮንም በተለይ የ6ኛ እና 8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተናዎችን የሚያርም ሲስተም አበልፅጎ ማስተላለፉ ይታወሳል። መሰል ተቋማዊ የትብብር ስራዎችን መስራት የሚያስችል ስምምነት ደግሞ ዛሬ በሁለቱ ተቋማት ተፈርሟል።
የመግባቢያ ስምምነቱን የፈረሙት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም እንደተናገሩት ‘’የትምህርት ጥራት እንደሀገር ትልቅ ትኩረት ተሰቶት እየተሰራ ሲሆን የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲም በተለይ ከትምህርት ዘርፉን በቴክኖሎጂ የማዘመን፣ የመምህራን እና ተማሪዎች ስልጠና እንዲሁም ትምህርት ቤቶችን የማደስ እና የማጣቀሻ መፅሃፍትን በማበርከት ሰፊ ስራዎችን እየሰራ ቆይቷል’’ ብለዋል።
የትምህርት ዘርፉን ስብራት ለማከም የሁሉንም ተቋማት እና የዘርፉን ምሁራን ርብርብ ይፈልጋል ያሉት ዶ/ር ኡባህ አደም የትምህርት ጥራንትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራትን በመለየት፣ በማቀድ እና ተከታታይ ድጋፍ እና ክትትል በማድረግ ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ሱልጣን አሊዪ በበኩላቸው የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ አሰራሮችን የሚያዘምኑ ቴክኖሎጂዎችን ለትምህርት ቢሮ ማበርከቱን በማስታወስ ዩኒቨርሲቲው እገዛ ምስጋና አቅርበዋል። የትምህርት ቢሮ ሃላፊው በማከልም በሁለቱ ተቋማት መሀል የተደረገው ስምምነት ከዚህ በፊት የነበረውን ትብብር ከማጠናከሩም በላይ አስተዳደሩ ከትምህርት ጥራት ጋር ተያይዞ ለሚሰራቸው በርካታ ስራዎች እገዛ የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመዋል።
Share This News